የባህር በር ለኢትዮጵያ መግቢያና መውጫዋ ብቻ ሳይሆን እስትንፋሷ ጭምር መሆኑን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት አምባሳደር ቶፊቅ ሬድዋን እና አምባሳደር ዲና ሙፊቲህ ገለጹ፡፡
አምባሳደር ቶፊቅ በጉዳዩ ላይ በአንዳድ አካላት ጥያቄ መነሳቱ አግራሞትን መፍጠሩ ትክክለኛ እሳቤ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በንድፈ ሀሳብ ብቻ ሳይሆን ለዘመናት የባህር በር ባለቤት እንደነበረች አስታውሰው ፣ የባህር በር ባለቤት እያለች እና የባህር በር አልባ መሀል ያለው ልዩነት ስለሚታወቅ ጥያቄው መነሳቱ ተገቢና ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ እንዲፈታ የምትፈለገው በድርድር አልያም ሰጥቶ በመቀበል መርህ መሆኑን አንስተው ፣ 130 ሚሊዮን ህዝብ ፣ እያደገ ከመጣው ኢኮኖሚ ጋር ተደምሮ ያለ ባህር በር ኑሩ መባል አስቸጋሪ መሆኑን አምባሳደሩ ቶፊቅ ሬድዋን አመላክተዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባህር በር ፍላጎት ግልፅ የመብት ጥያቄ ፣ የህልውና ጉዳይ ፣የእድገት እና ብልፅግና ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል ።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ካላት ቁመና አንፃር ማለትም ከኢኮኖሚ፣ ከፖለቲካ፣ ከማህበራዊ፣ ከፀጥታ እና ከወታደራዊ ጉዳዮች አንፃር የባህር በር አስፈላጊነቱ አጠያያቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ደረጃ የሚገኝ በአለም አቀፍ ደረጃ የባህር በር የሌለው አገር የለም ያሉት አምባሳደሩ፣ይህም የባህር በር አስፈላጊነቱን ፈንትው አድርጎ ያሳያል ብለዋል ።
የአለም አቀፍ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ምሁር አቶ ጥላሁን ሊበን ፣ አለም አቀፍ ግንኙነት በማጠናከር እና በአገር አቀፍ ደረጃ በሚደረግ ጥረት ደግሞ ብሄራዊ ጥቅምን የሚሳካባቸው መንገዶች መሆናቸውን ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለቀጠናው እድገት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
ይህንንም ሲያብራሩ ኢትዮጰያ በምታገኘው የባህር በር የባህር ሀይል በመመስረት የቀጠናውን ሰላም ለማስፈን በእጅጉ ጠቃሚ መሆኑን ያስረዳሉ።
የባህር ላይ ውንብድናዎችን ለመከላከል እና የአገር ሉአላዊነተ ለማስከበር የባህር በር ያስፈልጋል ያሉት ምሁሩ ፣ቀጠናውን የሚያምሱ እንደ አልሸባብ አና መሰል አሸባሪ ቡድኖችን አደብ ለማስገዛት ያግዛል ብለዋል።

በተጨማሪ ለጎረቤት አገሮችም ኢትዮጰያ የባህር በር ቢኖራት በእጅጉ የሚያተርፉ ስለመሆናቸው አብራርተዋል፡፡
እንደ ሀገር የባህር በር የዜጎች ጉዳይ መሆኑን በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጰያውያን ፣ የአካዳሚክ ተቋማት ፣ የሲቪክ ማህበረሰብ፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እንዲሁም መገናኛ ብዙሃን በሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ የድርሻቸውን መወጣት አለባቸው ብለዋል።
የባህር በር ጉዳይ ታሪካችን ነው የሚሉት ምሁሩ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘት ብቻ ሳይሆን ሌሎች ጉዳዮችን የማስፈፀም አቅም እና ጉልበት እንዳላት ገልፀዋል።
ይህንን ማድረግ የሚቻለው ግን ሀገራዊ አንድነት እና አገራዊ ደህንነት ስንፈጥር ነው ያሉት አቶ ጥላሁን ፣ ይህንን ለመሳካት ዜጎች አገራዊ ፍቅር ሲያዳብሩ እና ከመንግስት ጋር በትብብር መስራት ሲቻል ነው ሲሉ መፍትሔ የሚሉትን ሀሳብ አቅርበዋል።
በሔለን ተስፋዬ