ትንሹ ልጄ ነዉ ከሞት አፋፍ የታደገኝ – ጃራ ሰማ (ዶ/ር)

You are currently viewing ትንሹ ልጄ ነዉ ከሞት አፋፍ የታደገኝ – ጃራ ሰማ (ዶ/ር)

AMN ህዳር 17/2018

በተሽከርካሪ አደጋ ከደረሰባቸዉ ከባድ የአካል ጉዳት ለማገገም መድሃኒት በመዉሰድ ላይ ነበሩ፤ ነገር ግን መድሃኒቱ እንዴት ወደ ሱስ ሊሸጋገር ቻለ?

ጃራ ሰማ (ዶ/ር) በአንዲት አጋጣሚ ከደረሰባቸዉ የተሽከርካሪ አደጋ ለማገገም ከጤና ባለሙያዎች የታዘዘላቸዉን መድሃኒት በተደጋጋሚ በመዉሰድ ላይ እያሉ ወደ ሱስ እንደተቀየረባቸዉ ያስረዳሉ፡፡

“በመርፌ መልክ ስወስድ የነበረዉ መድሃኒት ይሰማኝ የነበረዉን ህመም ሲያሽለኝ ስለነበረ ለረጅም ጊዜአት ተጠቀሜአለሁ; ህመሙ ቢጠፋም ሰዉነቴ ግን መድሃኒቱን እንድጠቀም ያስገድደኛል፤ በኋላ ላይ ግን ጉዳዩ ሱስ መሆኑን ተረድቻለሁ” ሲሉ ባለታሪካችን ከኤኤምኤን ፕላስ ካሪቡ ፕሮግራም ጋር በነበራቸዉ ቆይታ አስረድተዋል፡፡

ጃራ ሰማ (ዶ/ር) ከዚህ ገጠመኝ በመነሳት እና ጉዳዩን መነሻ በማድረግ በአማርኛ እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች ከሱስና ከሱሰኝነት ነጻ መሆን በሚቻልበት ጥበብ ዙሪያ መጽሃፍ ማሳተማቸዉን ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መጽሃፋቸዉ የመድሃኒት ሱስ ያስከተለባቸዉን ተጽእኖ በዝርዝር አስፍረዋል፡፡

“ለመፈወስ ብዬ ስወስደዉ የነበረዉ መድሃኒት ጤንነቴን ጎድቶታል፤ ወሳኝ የሚባሉ የሰውነት ክፍሎቼን ለከፋ ጉዳት ከማጋለጡ በላይ በሞት አፋፍ ላይ ደርሼ ነበር”ይላሉ ጃራ ሰማ (ዶ/ር)፡፡

“ከዚህ በኋላ አንዲት መርፌ ብትወስድ ትሞታለህ ቢሉኝ መዉሰድን እመርጣለሁ፡ አንድ ቀን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለሁ ትንሹ ልጄ በድንገት ደርሶ ከሞት አፋፍ አድኖኛል “ሲሉ በእምባ በታጀበ ስሜት ተናግረዋል፡፡

“መድሃኒቱን ከወሰድክ ትሞታለህ፤ እኔ ደግሞ አባት አጣለሁ” በማለት ልጄ ሲማጸነኝ በክንዴ ላይ የተወጋሁት መርፌ እጄ እየደማ ከመድሃኒት ጋር ነቅዬ ጣልኩት ሲል ገልጸዋል፡፡

“ትንሹ ልጄ አባቴ ከዚህ በኋላ አይሞትም” በማለት ለሁሉም ሰዉ ተናገረ፡፡

ከዚህ አጋጣሚ በኋላ ጃራ ሰማ (ዶ/ር) ወዲያዉኑ ጤና ባለሞያዎች ጋር በመደወል ” የማገገም ህክምና መጀመር እፈልጋለሁ” በማለት ያሳወቁ ሲሆን ከሱሱ ካገገሙ 10 አመት እንደሞላቸዉ ገልጸዋል፡፡

ዜጎች በሱስ ምክንያት ከሚደርስባቸዉ ተጽእኖ እንዲያገግሙ ለማድረግ ፋዉንዴሽን አቋቁመዉ ወገናቸዉን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡

የተለያዩ ተቋማትን መስርተዉ በማስተዳደር ላይ የሚገኙት ጃራ ሰማ (ደ/ር) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባል በመሆን የመረጣቸዉን ህዝብ በማገልገል ላይ ናቸዉ፡፡

“ሱስ በቀላሉ ይጀመራል፤ ግን ሱስ በሽታ ነዉ ፤ ቢሆንም ግን ከሱስ መላቀቅ ይቻላል” ሲሉ ይመክራሉ፡፡

ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለዉ ሌላ መጽሃፍ ማሳተማቸዉን የጠቆሙት ባለታሪካችን ወላጆች ልጆቻቸዉ በሱስ እንዳይጠመዱ ብርቱ ክትትል ማድረግ እንደሚጠበቅባቸዉ መክረዋል፡፡

በዜጎች ላይ በተለይም በወጣቶች ላይ የሚታየዉን የሱሰኝነት ችግር ለመከላከል መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባልም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኮሪደር እና ወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ያከናወናቸዉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ዜጎችን ከአልባሌ ቦታዎችና ከሱስ ለመታደግ በእጅጉ ያግዛል፡፡

‎የሱስ ማገገሚያ ማእከላትን ከማብዛት ይልቅ ወጣቶች የሚዝናኑባቸዉን ስፍራዎችና የስፖርት ማእከላትን በስፋት መገንባት እና ወጣቶችን ለሱስ የሚያጋልጡ ከባቢዎችን ማጽዳት ጠቃሚ መሆኑንም ጃራ ሰማ (ደ/ር) ለኤኤምኤን ገልጸዋል፡፡

‎በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚገኙ እና ወጣቶችን ለሱስ የሚያልጡ ስፍራዎችን ለማስወገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጀመራቸዉ እርምጃች ትልቅ ተምሳሌትንት ስላላቸዉ በየቦታዉ ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል፡፡

የመድሃኒት መደብሮች ሳይቀሩ የትምህርት ተቋማት ካሉባቸዉ አካባቢዎች እንዲርቁ ቢደረግ የተሻለ መሆኑም መክረዋል፡፡

በተገኝ በፍቃዱ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review