በታይላንድ ደቡባዊ ክፍል በደረሰውና የ33 ሰዎችን ህይወት ከቀጠፈው የጎርፍ አደጋ በሆስፒታል የሚገኙ ታካሚዎችን በሄሊኮፕተር ለማስወጣት ማቀዳቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ገልጸዋል፡፡

ጎርፉ በማሌዥያም ስምንት ግዛቶችን ሲያጥለቀልቅ፣ በታይላንድ ደግሞ ዘጠኝ ግዛቶችን በማጥለቀለቅ ከሁለቱም ሀገራት ወደ 45 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቀው እንዲወጡ ምክንያት ሆኗል።

በኢንዶኔዥያም፣ በዚህ ሳምንት በጎርፍ እና በመሬት መንሸራተት አደጋ ምክንያት እስከ አሁን 13 ሰዎች ህይወታቸው ሳያልፍ እንዳልቀረ የተገለጸ ሲሆን፣ በማሌዥያ ደግሞ አንድ ሰው ህይወት ማለፉ ተገልጿል።
በታይላንድ በጣም በተጎዳችው ሃት ያይ ከተማ፣ አንድ የሕዝብ ጤና ባለሥልጣን ሄሊኮፕተሮች ምግብ እንደሚያደርሱ እና ታካሚዎችን እንደሚያጓጉዙ ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኝ ትልቅ የመንግሥት ሆስፒታል የመጀመሪያ ፎቅ ላይ 600 ሰዎችን ህክምና የሚሰጥ ሲሆን፣ 50 የሚሆኑት በከፍተኛ እንክብካቤ ውስጥ ይገኛሉ።
ይሁንና “ዛሬ፣ ሁሉም ከፍተኛ እንክብካቤ ውስጥ የሚገኙ ታካሚዎች፣ ከሃት ያይ ሆስፒታል ይወሰዳሉ” ሲሉ የሚኒስቴሩ ባለሥልጣን ሶምሬክ ቹንግሳማን ለሮይተርስ ተናግረዋል።
በታምራት ቢሻው