ዩክሬን አሜሪካ ባቀረበችዉ የሰላም እቅድ ላይ መግባባት ላይ መደረሷን ገልጻለች፡፡
የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልዑካንም የሩሲያዉ ፕሬዝዳንት ቫላድሚር ፑቲንን ሊያገኟቸዉ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር የምታደርገዉን ጦርነት ለማስቆም ከአሜሪካ ጋር በሰላም ስምምነቱ ላይ የተለመደ መግባባት ላይ መድረሷን ነዉ የገለጸችዉ፡፡
ይህ የሰላም ሀሳብ አሜሪካ ለኪየቭ ባቀረበችው ባለ 28-ነጥብ እቅድ ላይ የተመሠረተ መሆኑም ተገልጿል፡፡
የአሜሪካ እና የዩክሬን ባለሥልጣናት በዚሁ የሰላም እቅድ ዙሪያ ባለፈዉ ሳምንት በጄኔቫ ድርድር ማካሄዳቸዉ ይታወሳል፡፡
የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት፣ የመጀመሪያው እቅድ ተጨማሪ ግብዓት ከሁለቱም ወገን የተጨመረበት እና በጥሩ ሁኔታ የተስተካከለ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የእርሳቸው ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት ስቲቭ ዊትኮፍን በሚቀጥለው ሳምንት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን ሞስኮ ላይ እንዲያገኙ ትእዛዝ መስጠታቸዉንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይሎች ሚኒስትር ዳን ድሪስኮል ደግሞ በዚሁ ሳምንት የዩክሬንን መሪዎች ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ አወዛጋቢ ናቸዉ በተባሉ ነጥቦችን ዙሪያ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን፣ የእሳቸው አስተዳደርም ወሩ ከመጠናቀቁ በፊት በዚህ ጉዳይ ላይ ስብሰባ ለማድረግ እየጣረ መሆኑን ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ዜለንስኪን እና ፑቲንን በቅርቡ አገናኛቸዋለሁ ያሉት ዶናልድ ትራምፕ፣ ጦርነቱን ለማስቆም እየተደረገ ያለዉ ስምምነት ዉጤታማ የሚሆነዉ ጉዳዩ ፍጻሜ ላይ ሲደርስ ብቻ ነው ማለታቸዉን ቢቢሲ ጨምሮ ዘግቧል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ