በሆንግ ኮንግ የመኖሪያ ህንፃዎች ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ የ44 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፣ 45 ሰዎች በአስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ እና ሌሎች 279 ሰዎች እስካሁን አለመገኘታቸው ተገልጿል፡፡
የእሳቱ መንስኤ አሁንም እየተጣራ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ፣ ህንፃዎቹ እድሳት እየተደረገላቸው እንደነበር ጠቅሶ፣ በህንፃዎቹ መስኮቶች ላይ መረብ እና የፕላስቲክ ወረቀቶች መገኘታቸውን አመላክቷል።
እነዚህ ቁሳቁሶችም እሳቱ በፍጥነት እንዲዛመት አስችለውት ሊሆን ይችላል ሲልም ፖሊስ ገልጿል።

በእሳት ከተያያዙት ስምንት ህንፃዎች ውስጥ የአራቱን መቆጣጠር የተቻለ ቢሆንም፣ አሁንም ከአንዳንዶቹ ህንፃዎች ውስጥ ጭስ ሲወጣ መታየቱ ተገልጿል፡፡
የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል እሳቱን ለመቆጣጠር ሙሉ ቀን እንደሚፈጅበት ግምቱን አስቀምጧል፡፡
አደጋውን ተከትሎ በመቶዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሕንጻዎቹን ለቀው ወደ ድንገተኛ መጠለያዎች ሄደዋል፡፡

የሆንግ ኮንግ የእሳት አደጋ መከላከያ ክፍል፣ እሳቱን እንደ ደረጃ አምስት እጅግ ከባድ ማንቂያ ደወል አድርጎ መድቦታል።
ለመጨረሻ ጊዜ በሆንግ ኮንግ ደረጃ አምስት የእሳት አደጋ የተከሰተው ከ17 ዓመታት በፊት ነበር።
በታምራት ቢሻው