የተነቃቃ ለውጥና ዕድገት እያስመዘገበች ያለችው አዲስ አበባ ከተማ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ያላትን ስፍራ ማላቅ የሚያስችሉ ስኬቶችን እያገኘች መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በሰሞነኛ ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
ተከታታይ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ መድረኮችን እያስተናገደች ያለችው አዲስ አበባ በዓለም ሀገራት ዘንድ ተወዳጅ እና በዓለም አቀፍ ተቋማትም ተመራጭ እየሆነች ስለመሆኗ አንስተዋል።
ከተማዋ እያስተናገደቻቸው ካሉ አህጉራዊና ዓለም አቀፍ ሁነቶች ባሻገር የበርካታ ሀገራትና ተቋማት ማዕከልነት ተመራጭ እየሆነች ትገኛለች።
መሪዎች፣ የተቋማት አመራሮች ፣ ጎብኝዎች እየተመላለሱባት ያለችው መዲናዋ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ይበልጡን ተጠናክሮ ቀጥሏልም ነው ያሉት፡፡

ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የሆኑት የማሌዥያና ሲንጋፖር መሪዎች የሰሞኑ ይፋዊ ጉብኝት አንዱ ማሳያ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት አዲስ አበባ እንግዳ የነበሩት የሲንጋፖሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሎውረንስ ዎንግ ሀገራቸው በአዲስ አበባ ኤምባሲ ለመክፈት መወሰኗን አስታውቀዋል ብለዋል።
ከሲንጋፖር ባሻገር ማሌዥያ፣ ስሎቫኪያና ኢንዶኔዥያ በአዲስ አበባ ኤምባሲ ለመክፈት ውሳኔ ላይ ስለመድረሳቸው ይፋ አድርገዋል።
ከዚህ ቀደምም ስሎቬኒያና ኮሎምቢያ ኤምባሲያቸውን በአዲስ አበባ መክፈታቸውን አውስተዋል።
በዚህም 6 አዳዲስ ኤምባሲዎችን ጨምሮ አዲስ አበባ ከ140 በላይ ሀገራት ቋሚ መቀመጫ ትሆናለች።
በአቡ ቻሌ