ከቀዶ ህክምና በፊት እና በኋላ መደረግ ስላለባቸው የጤና ጥንቃቄዎች ምን ያህል ያውቃሉ?

You are currently viewing ከቀዶ ህክምና በፊት እና በኋላ መደረግ ስላለባቸው የጤና ጥንቃቄዎች ምን ያህል ያውቃሉ?
  • Post category:ጤና

AMN ህዳር 19/2018

የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስት ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ቤካ ገቢሳ ታካሚው የቀዶ ህክምና ከማድረጉ በፊት ቀዶ ህክምና ለምን እንደሚያስፈልግ፣ በሽታው ምን እንደሆነ? ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል በሂደቱ ምን ሊያጋጥም እንደሚችል በደንብ መረዳት እንደሚኖርበት ከ ኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል፡፡

ከቀዶ ህክምና በፊት እና በኋላ በታካሚው እና በሀኪሞች መደረግ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች የገለጹት ዶ/ር ቤካ የቀዶ ህክምና በሁለት እንደሚከፈል እና ይህም ታስቦበት የሚደረግ እና በድንገት የሚደረግ ቀዶ ህክምና እንደሆነ ተናግረዋል።

ከቀዶ ህክምና በፊት መደረግ ያለባቸው ጥንቃቄዎች

ከቀዶ ህክምና በፊት ታካሚው ጤንነቱ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እና ለቀዶ ህክምና ብቁ መሆኑን ለማወቅ ምርመራ እንደሚደረግለት ገልጸዋል።

በዚህም ከሰመመን መድሃኒት ጋር የተገናኙ ህመሞች ካሉ፣ ከልብ በሽታ፣ ከደም ግፊት፣ የስኳር በሽታ፣ የመድማት ችግር፣የሳምባ በደንብ መተንፈስ መቻሉን እና ንጹህ መሆኑን በመመርመር ለሚደረግበት ቀዶ ህክምና ብቁ መሆኑን ከተረጋገጠ በኋላ ፍቃደኝነቱ እንደሚጠየቅ ገልጸዋል።

አንድ ታካሚ በእቅድ ቀዶ ህክምና ሊደረግለት ሲል ሙሉ በሙሉ የሰመመን መድሀኒት የሚወስድ ከሆነ ከቀዶ ህክምናው ከመደረጉ በፊት ባሉት ረጅም ሰዓታት መመገብ እንደሌለበት ገልጸዋል።

ይህም ታካሚው የሰመመን መድሃኒት ሲወስድ እራሱን ስለማያውቅ ምግብ ተመግቦ ከሆነ ወደላይ ስለሚለው እና ምግቡ ሳምባው ውስጥ ገብቶ ችግር ሊፈጥርበት ስለሚችል እንዳይመገብ ይከለከላል።

ከቀዶ ህክምና በኋላ መደረግ የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

ቀዶ ህክምና የተደረገለት ታማሚ ከሰመመን ሙሉ በሙሉ እስከሚነቃ ድረስ በቀዶ ህክምና ክፍል/ሪከቨሪ ክፍል/ ውስጥ አተነፋፈሱ፣ የልብ ምቱ ሌሎች የጤና ሁኔታዎችም መስተካከላቸው እንደሚታይ እና በጣም በከፍተኛ ጥንቃቄ ክትትል እንደሚደረግለት ገልጸዋል፡፡

ከቀዶ ህክምና በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮች

ታማሚው ከቀዶ ህክምና በኋላ ብዙን ጊዜ የሳንባ ኢንፌክሽን፣ በደንብ አለመተንፈስ፣ በተለይ ሆድ ላይ ቁስል ካለ ለመተንፈሰ መቸገር ሊኖር እንደሚችል ለዚህ ደግሞ ማስታገሻ እንደሚሰጥ እና ታማሚዎች መፍራት እንደሌለባቸው ጠቅሰዋል።

ታማሚዎች ከቀዶ ጥገና በኋላ አስለው አክታቸውን የማይተፉ ከሆነ፤ ለሳንባ ምች ህመም እንደሚጋለጡ፤ እና ይሄ እንዳይሆን አየር በደንብ ስበው ወደ ውጩ ማስወጣት እና አስለውም አክታ ካለ በመትፋት ሳንባቸውን ንጹህ ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በቀዶ ህክምናው የቆሰለው የሰውነት ክፍል ኢፌክሽን እንዳይፈጥር ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ይህም መሸፈን ካለበት ተሸፍኖ እንዲቆይ ማድረግ፣ ከቆሻሻ ጋር ንክኪ እንዳይኖር እና በእንቅስቃሴ ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ታካሚው ቀዶ ጥገና ካደረገ በኋላ የሚተኛ ከሆነ ለደም መርጋት ይጋለጣል ስለዚህ በተቻላቸው መጠን እቅስቃሴ ማድረግ እንደሚኖርበት አመላክተዋል።

ሌላው ከቀዶ ህክምና በኋላ መደረግ ካለባቸው ጥንቃቄዎች መካከል አንዱ የሀኪሙን ምክር መስማት እና በአግባቡ ክትትል ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review