የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ ባለፉት የለውጥ ዓመታት እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓትን ለመገንባ የተከናወኑ ስራዎች ተጨባጭ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል፡፡
አፈ-ጉባዔው አክለውም፣ የፌዴራሊዝም ስርዓት ህዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር መብታቸውን ያረጋገጠ መሆኑን ጠቁመው፣ ይህም የእውነተኛ ፌዴራሊዝም ስርዓት አንዱ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሀገሪቱ የፌዴራሊዝም ስርዓት በመከተሏ ህዝቦች እራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ እና በቋንቋቸው እንዲተዳደሩ ማስቻሉን የገለጹት አፈጉባዔው፣ በማንነት እና በኢትዮጵያዊነት መካከል ያለን ሚዛን ማስተካከል ተችሏል ብለዋል፡፡
በተለይም የለውጡ መንግስት እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት በተጨባጭ መሬት እንዲይዝ ያላሰለሱ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየቱንም አብራርተዋል፡፡
ሀገራዊ ለውጡ በልማት እና በሰላም ካስመዘገባቸው ውጤቶች በተጨማሪ እውነተኛ ፌዴራሊዝምን መሬት ከማስያዝ አኳያ እመርታ መገኘቱንም አቶ አገኘሁ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት አይነት ጫፎች መኖራቸው የጠቆሙት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ አቶ አገኘሁ፣ እነዚህም የተነጣይነት አስተሳሰብ እና የጠቅላይነት አመለካከት መሆናቸውን አብራተዋል፡፡
ሁለቱም ሀሳበች ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን አይጠቅሙም ያሉት አፈ ጉባዔው፣ ነገር ግን ህብረ ብሄራዊ አንድነት ማረጋገጥ የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እና እኩልነትን ትሩፋቶችን የሚያስገኝ ነው ብለዋል፡፡
በህብረ ብሄራዊነት ውስጥ የሁሉም ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች እኩልነት የተረጋገጠባት ኢትዮጵያን መፍጠር እደሚገባ እና ለዚህም እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ወቅቱ ህዝዞች ለብሄራዊ ጥቅሞች በጋር የቆሙበት መሆኑን የገለጹት አቶ አገኘሁ፣ ለዚህም በባህር በር ጥያቄ ላይ የተያዘው አቋም ይጠቀሳል ብለዋል፡፡
20ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ቀን ”ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ ብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ በሆሳዕና ከተማ እንደሚከበርም ተገልጿል፡፡
በሀብታሙ ሙለታ