የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊነትን የአስተዳደርና የአንድነት መሰረት በማድረግ የጋራ ደህንነትና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገለጹ

You are currently viewing የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊነትን የአስተዳደርና የአንድነት መሰረት በማድረግ የጋራ ደህንነትና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገለጹ
  • Post category:አፍሪካ

AMN – ህዳር 19/2018 ዓ/ም

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ በአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊነትን የአስተዳደርና የአንድነት መሰረት በማድረግ የጋራ ደህንነትና ብልፅግናን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልፀዋል ።

4ኛው የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች እና መሰል ተቋማት ዓለም አቀፍ ሲምፖዝየም በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።

ሲምፖዚየሙ “ሕገ መንግሥታዊነት እና ሀገረ መንግሥት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ ነው እየተካሄደ ያለው።

በመድረኩ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የፍትሕ ሚኒስትር ሀና አርዓያ ሥላሴ፣ የአባል ሀገራቱ የሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶች ፕሬዝዳንቶች፣ ተጋባዥ በዓለም አቀፍ ተቋማት የሚሠሩ የዘርፉ ምሁራን እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ሥስላሴ በዚሁ ወቅት፥ የሕገ መንግሥታዊነት ጽንሰ ሀሳብ ሕጎችን ማውጣት ብቻ አለመሆኑን ገልጸዋል።

የሕግ የበላይነትን ማስፈን፣ የተጠያቂነትን መርህን መዘርጋት እና ለመሠረታዊ መብቶች አክብሮት መስጠትን የሚመለከት መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ሥልጣን በሕግ ወሰን ውስጥ መተግበር እንዳለበት የሚገልጽ የሞራል ግዴታ እና መርሆዎች ስብስብ መሆኑን አመላክተዋል።

ይህ ሕጋዊነት ለመንግሥታዊነት መሠረታዊ መስፈርት እና መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ የዜጎችን ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች ለማረጋገጥ የሚያገለግል ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥታዊነት የተለየ ልምድ ያላት ሀገር መሆኗን ጠቅሰው፤ በንጉሣዊ ስርዓት የነበረው የፍትሐ-ነገሥት እንዲሁም እንደገዳ ስርዓት ያሉ ሀገር በቀል የሕግና አስተዳደር ስርዓቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ሕገ መንግሥት ያላት ሀገር መሆኗን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ፥ አሁን ያለው ሕገ መንግሥት ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ትኩረት የሰጠ የሕግ የበላይነት ምሰሶ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሌላ በኩል አፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ አስተዳደርን ለማስፈን የምታደርገው ጥረት የተለያዩ ተግዳሮቶች እያጋጠሙት እንደሚገኝ አንስተዋል።

ስልጣንን በሕገ መንግሥታዊ ስርዓትና በህዝብ ድምፅ ከማግኘት ይልቅ በመፈንቅለ መንግሥትና በተቃውሞ የማግኘት ዝንባሌ በአህጉሪቱ ከሚገጥሙ ችግሮች መካከል መሆኑን ተናግረዋል።

የፖለቲካ አለመረጋጋት፣ ተቋማዊ አቅም ማነስና ሕገ መንግሥታዊ ስርዓትን ያልተከተለ ስልጣን የማግኘት ፍላጎት ለአህጉሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ጉዞ ፈተና የሆኑ ተግዳሮቶች መሆናቸውንም የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።

በመሆኑም በአፍሪካ የጋራ ደህንነት እና ብልጽግናን ለማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊነትን የአስተዳደርና የአንድነት መሰረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review