አዲስ አበባ ከተማን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በዘርፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

You are currently viewing አዲስ አበባ ከተማን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በዘርፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

AMN – ህዳር 19/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ከተማን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ በዘርፉ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዮሀንስ ጫላ ተናግረዋል።

ኃላፊው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ የነባር ሆስፒታሎችን ደረጃ ከማሳደግ ባለፈ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ሊሆኑ የሚችሉ ዘመናዊ ሆስፒታሎችን ግንባታ አጠናቅቆ ወደ አገልግሎት ለማስገባት በሂደት ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ እና በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ እየተገነቡ ያሉ ሆስፒታሎች እያንዳንዳቸው ከ5 መቶ በላይ አልጋዎችን መያዝ የሚችሉ መሆናቸውን የጠቀሱት የቢሮ ኃላፊው፣ የጥራት ደረጃቸውም ዓለም አቀፋዊ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ገላን አካባቢ የተገነባው እና ከ5 መቶ 11 በላይ አልጋዎች ያሉት ሆስፒታልም፣ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመሪያው ሊሆን እንደሚችል እና ይህም ከተማዋን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተጀመረውን ጉዞ እውን ለማድረግ ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የቢሮ ኃላፊው አክለው፣ ረጅም እድሜ ያስቆጠሩ የዘውዲቱ እና የራስ ደስታ ሆስፒታሎችን ጨምሮ ሌሎችንም በማደስ፣ ግዙፍ ዘመናዊ ሆስፒታሎች በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡

በእነዚህ ሆስፒታሎች እያንዳንዱ ታካሚ በቂ ኦክስጅን እንዲያገኝ ለማስቻል ኦክስጅንን ከማምረት ጀምሮ ሌሎች የህክምና ግብዓቶችም ተሟልተው መገንባታቸውን ተናግረዋል፡፡

የግሉን የጤና ዘርፍ ለማበረታታትም ለጤና ተቋማት ግንባታ የሚውል የመሬት አቅርቦት በመደረጉ ሰፋፊ ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review