የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በልዩነት ውስጥ አንድነትን በመገንባት በመቻቻልና በአብሮነት የምናከብረው በዓል መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ማሾ ኦላና ተናገሩ።
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ተከብሯል።
ዘንድሮ ቀኑ ለ20ኛ ጊዜ ”ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለሕብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል።
በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በተከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ማሾ ኦላና በዓሉ በሁሉም መስክ የሀገራችንን ከፍታ እያረጋገጥን ባለንበት ወቅት እየተከበረ የሚገኝ ነው ብለዋል።
እንደሀገር ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ እና በስንዴ ልማት ባስመዘገብናቸው ስኬቶች እንዲሁም እንደ አዲስ አበባ ከተማም በኮሪደር እና በወንዞች ዳርቻ ልማት ስኬቶች ባስመዘገብን ማግስት በዓሉን ማክበራችን ለየት ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል ።
የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በልዩነት ውስጥ አንድነትን በመገንባት በመቻቻልና በአብሮነት የምናከብረው በዓል ነው ሲሉም ነው አቶ ማሾ የተናገሩት።
በዓሉ በክፍለ ከተማው ብሔር ብሔረሰቦችን በሚወክሉ ልዩ ልዩ የባሕል አልባሳትና ትርኢቶች ታጅቦ በድምቀት ተከብሯል።
ታምሩ ደምሴ