የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን የሚያሰራጯቸውን ይዘቶች አሰመልክቶ ያወጣዉ መግለጫ እንደሚከተለዉ ቀርቧል
በሀገራችን የሃይማኖት እና የእምነት ነጻነት በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግሰት መረጋገጡ ይታወቃል፡፡ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ቁጥር 1238/13 መሰረት የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ምዕመኖቻቸው ባሉበት ሆነው በመገናኛ ብዙኃን አስተምህሮቶቻቸውን እንዲከታተሉ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃድ ወስደው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡
ባለስልጣኑ በአዋጁ በተሰጠው ኃላፊነት መሰረት መገናኛ ብዙኃን ተግባሮቻቸውን ህግና ሙያዊ ስነ-ምግባርን ባከበረ አግባብ ስለማከናወናቸው ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ክፍተቶች እንዲታረሙ ግብረ መልስ ይሰጣል ፣ እንደ ጥፋቶች ዓይነትም ተገቢውን አሰተዳደራዊ እርምጃ ይወስዳል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ለጂስስ ፕሮፌቲክ ስፕሪት ቸርች (ጂፒኤስ የቴሌቪዥን ጣቢያ) በቀን 13/4/2018 ዓ.ም በማህበራዊ ገጾቹ ላይ ያሰራጨውን ፕሮግራም ከመገናኛ ብዙኃን አዋጅ 1238/13 እና አግባብነት ካላቸው ህጎች አንጻር የክትትል ስራዎችን ያከናወነ ሲሆን በዚህም ፕሮግራሙ በሀገራችን የሰላሌ አካባቢን ተገቢ ባልሆነ መልኩ መገለጹን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡
በዚህም መሰረት ለጂፒኤሰ የቴሌቪዥን ጣቢያ በመገናኛ ብዙኃን አዋጅ የተጠቀሱ የህግ ድንጋጌዎችን በመጣሱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።
በቀጣይም ከላይ የተጠቀሱትን ህጎች ጥሰው የተገኙ የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ላይ አስፈላጊውን እርምጃ የሚወስድ ሲሆን መገናኛ ብዙኃኑ ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ተገንዝበው በጥንቃቄና በኃላፊነት መንፈስ እንዲሰሩ ያሳስባል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለሥልጣን