ጥበብን ምን ያሳድገዋል ቢባል ምቹ የሥራ ቦታ፣ የተማረና ተሰጥዖ ያለው ባለሙያ እና ፖሊሲ አንድ ላይ ተደምረው ነው።
ለዚህ ነው ለጥበብ ዕድገት ትምህርት፣ ፖሊሲና ምቹ የሥራ ቦታ አስፈላጊ ናቸው የሚሉት የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ።
ሚኒስትር ዴታው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ጥበብ የምንሠራባቸው ቦታዎች ምቹና ዘመናዊ በሚሆኑበት ጊዜ ጥበብ የበለጠ እንዲያድግ ዕድል እንደሚሰጥ ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ ሜጋ አምፊ ቲያትር ብቻ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ከሀምሳ በላይ አምፊ ቲያትሮች ተገንብተዋል።
በተጨማሪም በመዲናዋ ከ120 በላይ በሚሆኑ ፓርኮች ውስጥ የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ሥራዎች የሚከናወኑባቸው ቦታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ የተሠሩ ቦታዎች መነሻ ሐሳባቸው ራሱ ጥበባዊ ይዘት ያለውና ውበት ላይ ትኩረት የሚያደርግ እንደሆነም ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
“ጥበብ የጋርዮሽ ነች፤ መገለልን፣ መለያየትንና ብቸኝነትን አትወድም። የጋራ ነገርን የሚያጠናክር ሁሉ የጥበብ ነው፤ በዚህም የተነሳ የሚመጣን የጠቆረና የጨለመ ነገር አትቀበልም” ብለዋል።
ጥበብ የጋራ ፍቅርንና በሕብረት የሚከናወኑ ሥራዎችን የምትወድ በመሆኗ፣ ይህንን በጋራ ለማከናወን ምቹ ቦታ እንደሚያስፈልግና ይህንንም ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሥራዎች በከተማዋ በስፋት መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ሚኒስትር ዲኤታ ነብዩ ባዬ ጥበብ የሚሰራባቸው ቦታዎች በቁጥር በዝተው እና በጥራት ልቀው ፤ ምቹና ዘመናዊ በሆነ መልኩ ለአገልግሎት እንዲበቁ በየደረጃው ያሉ የከተማ አስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ለነበራቸው ሚና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ፍሬሕይወት ብርሃኑ