ዓለማችን በካርታና በድንበር ብትከፋፈልም፣ የሰው ልጅን ልብና አዕምሮ ግን ማጠር አይቻልም። ሀገራት ሉዓላዊነታቸውን ለማስከበር በድንበር ላይ ወታደርና የጦር መሳሪያ ቢያሰልፉም፣ ካለምንም ተኩስና የኃይል እርምጃ የሰውን ልጅ መንፈስ ሰርጎ የሚገባ፣ ከወርቅና ከነዳጅ በላይ ሀገርን የሚያስተዋውቅ አንድ ትልቅ ሚስጥራዊ ሀብት አለ፤ እርሱም ኪነ-ጥበብና ባሕል ነው።
ይህ የማይጨበጥ ግን ደግሞ እጅግ ብርቱ የሆነ ሀብት፣ ሀገራት በጦር መሳሪያ ሳይሆን በልብና በአዕምሮ ላይ የበላይነትን የሚቀዳጁበት “ገር ኃይል” (Soft Power) እንደሆነ ይነገራል። የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ሰንኮፍ በተሸኘው ሳምንታዊው የቴሌቭዥን ፕሮግራሙ ላይ ያነጋገራቸው የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ፣ “የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚለካው በወታደራዊ ብዛት ወይም በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም” ይላሉ። ይልቁንም የሀገሪቱን ታሪክ፣ ስልጣኔና ማንነት በፈጠራ ሥራዎች ለዓለም ማሳወቅ የዘመናዊው ዲፕሎማሲ ዋነኛ መሣሪያ ሆኗል።

የጥበብ ተጽዕኖ ከሆሊውድ እስከ መርካቶ
ለዚህ “ገር ኃይል” ትልቁ ማሳያ አሜሪካ ናት። አሜሪካ በሆሊውድ ፊልሞቿ አማካኝነት ባሕሏንና ሉዓላዊነቷን ለዓለም ትሸጣለች። በፊልም የምናያቸው “ጀግኖች” ዓለም አሜሪካን የጀግኖች ምድር አድርጋ እንድታስብ በማድረግ ረገድ ትልቅ የሥነ-ልቦና ድል ተቀዳጅተዋል ብለው ያምናሉ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ)።
ሕንድም ብትሆን በፊልሞቿ አማካኝነት ቋንቋዋና ባሕሏ የኢትዮጵያ የንግድ ማዕከል እስከሆነው መርካቶ ድረስ እንዲሰርጉ አድርጋለች። ታዳጊዎቻችን ያለምንም መምህር ሕንድኛን የሚለምዱት በዚሁ የጥበብ ተጽዕኖ (ጥበባዊ ዲፕሎማሲ) ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ።
የኢትዮጵያ የጥበብ ጉዞ፡ ከንጉሡ እስከ ዛሬ

ኢትዮጵያ ይህንን የጥበብ ዲፕሎማሲ የመጠቀም ረጅም ታሪክ አላት። ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ወደ ተለያዩ ሀገራት በሚጓዙበት ወቅት ከያንያንን አስከትለው በመሄድ፣ የኢትዮጵያን የስልጣኔ ጥልቀትና የሙዚቃ ቅንብር ለዓለም ያስመሰክሩ ነበር። በደርግ ዘመንም ቢሆን፣ ወደ ምሥራቁ ዓለም (ሩሲያ፣ ቻይና እና ኩባ) የጥበብ ቡድኖች በመላክ የሀገርን ገጽታ የማስተዋወቅ ሥራ ይከናወን ነበር።
ከለውጡ በፊት እንደ ፍራንሲስ ፋልሴቶ ያሉ ግለሰቦች ከድምጻዊ መሐሙድ አሕመድ እና ዓለማየሁ እሸቴ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ዕውቅና የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል። ይሁን እንጂ፣ ጉዳዩን በመንግስት ደረጃ እንደ አንድ የፖሊሲ አካል በትኩረት መመልከት የተጀመረው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ይጠቅሳሉ።
“ኪን ኢትዮጵያ” እና አዲሱ ምዕራፍ

አገርን በታቀደና በተደራጀ መልኩ ለማስተዋወቅ “ኪን ኢትዮጵያ” የተባለ ንቅናቄ በመንግስት ደረጃ ተጀምሯል። ይህ ንቅናቄ ከመንግስት ባለፈ ተጽዕኖ ፈጣሪ አርቲስቶችንና የሚዲያ ሰዎችን በማሳተፍ ትልቅ ውጤት እያመጣ ይገኛል።
ለአብነት ያህል፣ በቅርቡ በቻይና የቀረበው የኪነ-ጥበብ ክንውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተመልካቾች ባላቸው ሶሻል ሚዲያዎች በቀጥታ ስርጭት መታየቱ የኢትዮጵያን መልካም ገጽታ ለዓለም ለማሳየት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ዛሬ ላይ ይህ የዲፕሎማሲ ዘርፍ በሙዚቃ፣ በፊልም፣ በሰርከስና በቁንጅና ውድድሮች ጭምር በስፋት እየተሠራበት ይገኛል።
ኢትዮጵያ ያላትን ጥልቅ ባሕልና ጥበብ በመጠቀም ይህንን “ገር ኃይል” ካጎለበተች፣ በዓለም መድረክ ላይ ያላትን ተጽዕኖ ፈጣሪነት ይበልጥ ማሳደግ እንደምትችል ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ። ጥበብ የድንበር አጥር የላትምና!
በሔለን ተስፋዬ