ሪዮ ዲ ጄኔሮ በአንድ ቦታ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በታደሙበት የዘመን መለወጫን በዓል በማስተናገድ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ሰፈረች

You are currently viewing ሪዮ ዲ ጄኔሮ በአንድ ቦታ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች በታደሙበት የዘመን መለወጫን በዓል በማስተናገድ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ ሰፈረች

AMN | ታኅሣሥ 23/2018 ዓ.ም.

የብራዚሏ ሪዮ ዲ ጄኔሮ የፈረንጆቹን 2026 ዓ.ም. ለመቀበል በኮፓካባና የባሕር ዳርቻ ያከናወነችው የዘመን መለወጫ በዓል በዓለም ላይ በከፍተኛ የሰው ቁጥር የተከበረ መሆኑ ተረጋግጦ በጊነስ ወርልድ ሪከርድ መመዝገቡ ተገለጸ።

የጊነስ ወርልድ ሪከርድ ባለሙያዎች በሰጡት መረጃ መሠረት፣ በዕለቱ በባሕር ዳርቻው ላይ ብቻ ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ታድመዋል። ይህም ከተሰብሳቢው ብዛት ባለፈ በዝግጅቱ ጥራት፣ በባሕላዊ እሴቱ እና በደኅንነት አጠባበቁ ተመዝኖ ክብረ ወሰኑን ሊያገኝ ችሏል።

የከተማዋ ከንቲባ ኤድዋርዶ ፓኤስ የክብረ ወሰን የምስክር ወረቀቱን በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፥ እንዲህ ያለውን ግዙፍ የሰው ቁጥር በየዓመቱ በስኬት ማስተናገድ የሚችሉ ከተሞች ጥቂት ናቸው። ሪዮም ይህን በማድረጓ ኩራት ይሰማታል ብለዋል።

በኮፓካባ ብቻ 2.5 ሚሊዮን ሰዎች ይሰባሰቡ እንጂ በመላው ከተማዋ እስከ 5 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በዓሉን ለማክበር ታድመዋል ተብሎ ይገመታል። በበዓሉ ዋዜማ ላይም 1 ሺህ 200 ድሮኖች የተቀናጀ የብርሃን ትዕይንት ያሳዩ ሲሆን፣ ለ12 ደቂቃዎች የሚቆይ የርችት ተኩስም ተካሂዷል።

ዝግጅቱ ቆሻሻን በአግባቡ በማስወገድ እና የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ባረጋገጠ መልኩ ተከናውኗል። በዝግጅቱ ላይም የታወቁ የብራዚል ሙዚቀኞች ሥራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ በዓሉ እስከ ንጋት ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች ደምቆ ቆይቷል።

ሁነቱ በበርካታ የዩቲዩብ ቻናሎች እና በሌሎች የማኅበራዊ ትስስር ገጾች በቀጥታ የተሰራጨ ሲሆን በቦታው ላይ የነበሩ ታዳሚዎችም የሚያጋሯቸው ፎቶዎችና ቪዲዮዎች ከተማዋን ያለምንም ክፍያ በዓለም ዙሪያ አስተዋውቀዋታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review