የጥበብ አበርክቶ ለብሔራዊ ጥቅም እስከ ምን?

You are currently viewing የጥበብ አበርክቶ ለብሔራዊ ጥቅም እስከ ምን?
  • ኪነ ጥበብ የሀገርን እውነተኛ መልክ ለዓለም በማሳየትና ዜጎችንም ለጋራ ዓላማ በማሰባሰብ ብሔራዊ
    ጥቅምን እንደሚያረጋግጥ ተጠቁሟል

የኪነ ጥበብ ስራዎች በሀገር ግንባታ ሂደት ውስጥ ምን አይነት ሚና አላቸው? የሚለው ጥያቄ ቶኒ ስኮት ዳይሬክት ባደረገው ቶፕ ገን (Top Gun) በተሰኘው ፊልም ውስጥ በግልጽ ተመልሷል፡፡ በተለይም በዝነኛው የፊልም ተዋናይ ቶም ክሩዝ በተወከለውና በዋና ገፀ ባህሪው ፒት ማቭሪክ ሚቸል በሚለው ስም ውስጥ ፍንትው ብሎ ይታያል። በ1986 የሆሊውድ ስክሪን ላይ ብቅ ያለው የተዓምረኛው አብራሪ ገፀ ባህሪ፣ የአሜሪካን ወታደራዊ ኃይል ከውድቀት ስነ-ልቦና አውጥቶ ወደ ጀግንነት ማማ ላይ ሰቅሎታልም ይባልለታል።

ማቭሪክ የፊልም ገጸ-ባህሪ ብቻ ሳይሆን፣ በሚሊዮኖች ልብ ውስጥ የሀገር ፍቅር እሳት የጫረና ወታደራዊ አገልግሎትን እንደ ፋሽን ያስቆጠረ የጥበብ ዲፕሎማሲ ውጤት ተደርጎም ይወሰዳል። እንዴት? የሚለውን ቀጥለን እንመልከት፡፡

በ1980ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የአሜሪካ ጦር ኃይል በቬትናም ጦርነት ሽንፈት ምክንያት በዜጎች ዘንድ ዝቅተኛ ተቀባይነት ነበረው። በዚህም ምክንያት ወጣቶች ወደ ውትድርና ለመቀላቀል ፈቃደኛ አልነበሩም። ‘ቶፕ ገን’ ለእይታ ከበቃ በኋላ፣ የአሜሪካ ባሕር ኃይል ብቻውን የ500 በመቶ የምልመላ ዕድገት ስለማስመዝገቡ የተቋሙ ሪፖርት ያመላክታል።

ፊልሙ የባሕር ኃይል አብራሪዎችን እንደ ጀግና አድርጎ በማሳየቱ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ፊልሙን ከማየት ወጥተው በቀጥታ ወደ ምልመላ ጣቢያዎች እንዲያመሩ አድርጓል ሲሉም የዘርፉ ባለሙያዎች ይመሰክሩለታል። ኤቢሲ ኒውስ ፊልሙን አስመልክቶ ባስነበበው ጽሑፍ የፊልሙ ገጸ ባህሪያት ወታደራዊ ሕይወትን እንደ አሰልቺና አደገኛ ስራ ሳይሆን፣ እንደ ፋሽንና እንደ ልዩ ክብር አድርጎ አቅርቦታል ሲል ያትታል። ብሔራዊ ጥቅም ማለት ሀገርን ከጥቃት መከላከል ብቻ ሳይሆን፣ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ ሀገርን ትልቅ አድርጎ መሳል ነውና ይህ ፊልምም ይህንን ዓላማ በመፈጸም ረገድ በታሪክ ውስጥ በምሳሌነት የሚጠቀስ የጥበብ ስራ ሆነ። 

በእርግጥም የፊልም ፀሐፊው ጃክ ኢፕስ ጁኒየር እንደሚሉት የአንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ሲባል ግዛታዊ አንድነትንና ኢኮኖሚን ብቻ ሳይሆን፣ የሀገሪቱን ገጽታ መገንባትና በዓለም አቀፍ መድረክ ተሰሚነትን ማሳደግም ጭምር ነው። በዚህ ረገድ የጥበብ ስራዎች ‘ገር ኃይል’ (Soft Power) በመባል የሚታወቁ እጅግ ረቂቅ ግን ደግሞ ብርቱ መሣሪያዎች ናቸው።

የጥበብ ስራዎች ዜጎች ስለ ታሪካቸው እንዲያውቁ፣ በሀገራቸው እንዲኮሩና ለብሔራዊ ጥቅሞችም በጋራ ዓላማ እንዲቆሙ ያነሳሳሉ። በአንድ ሀገር ግንባታና ህልውና ውስጥ ብሔራዊ ጥቅም የሚባለው ጽንሰ-ሀሳብ እንደ ምሰሶ የሚታይ ነው። ይህ ጥቅምና ፍላጎት በፖለቲከኞች ንግግርና በወታደራዊ ኃይል ብቻ የሚጠበቅ አለመሆኑን ደግሞ እንደ ቶፕ ገን ያሉ እውቅ ፊልሞችን በማሳያነት መጥቀስ ያስፈለገውም ለዚሁ ነው።

ብሔራዊ ጥቅም በሕዝብ ልብ ውስጥ የታረሰ፣ በዜጎች ንቃት የተቃኘና በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ እንዲሆን “ገር ኃይል” (Soft Power) ሚና ወሳኝ እንደሆነ የባህል እና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) በቅርቡ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። እዚህ ላይ ነው የኪነ ጥበብና የባለሙያዎቹ ፋይዳ የሚጎላው። ለ“ገር ኃይል” ትልቁ ማሳያ ተደርጋ የምትጠቀሰው ሀገር አሜሪካ ስትሆን በሆሊውድ ፊልሞቿ አማካኝነት ባሕሏንና ሉዓላዊነቷን ለዓለም ትሸጣለች። በፊልም የምናያቸው “ጀግኖች” ዓለም አሜሪካን የጀግኖች ምድር አድርጋ እንድታስብ በማድረግ ረገድ ትልቅ የሥነ-ልቦና ድል እደተቀዳጁም ብዙዎች ያምናሉ።

ጉዳዩን ወደ ኢትዮጵያ መለስ አድርገን የብሔራዊ ጥቅም እና ጥበብ ምንና ምን ናቸው? ብለን እንጠይቃለን፡፡ በተለይም አሁን ላይ ኢትዮጵያ የብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቂያ ከሆኑት ጉዳዮች ዋነኛ የሆነውን የባሕር በር ጥያቄ እያነሳች ባለችበት በዚህ ወቅት ይህንን ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ሆኖም ይህ ጥያቄ በሕዝቡ ዘንድ በስሜት ብቻ ሳይሆን በዕውቀትና በባለቤትነት መንፈስ እንዲያዝ የኪነ ጥበብ ሰዎች ምን ይስሩ የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ይሆናል፡፡

የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና እንጂ የቅንጦት ጥያቄ አለመሆኑንና እውን እንዲሆንም ኪነ ጥበብ የሚኖረው ድርሻ ከፍተኛ ስለመሆኑ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡ ድምጻዊ መምህሩ ጫሞም የሚለው ይህንኑ ነው፡፡ ደምጻዊው እንደሚያብራራው ባለሙያው ኪነ ጥበብን ተጠቅሞ ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የነበረች መሆኑን፣ ከዚህ ቀደም ከዓለም ጋር ትገናኝ የነበረበትን ታሪክ በፊልሞች፣ በቴአትሮችና በልብ ወለዶች መተረክ። “ይህም ዜጎች የጠፋባቸውን እንጂ የሌላቸውን እየጠየቁ እንዳልሆነ ግንዛቤ መፍጠር ይቻላል” ይላል ድምጻዊ መምህሩ ጫሞ።

የባሕር በር አለመኖር በየዕለቱ በኑሮ ውድነት ላይ የሚያሳድረውን ጫና በቀላል ስነ-ጥበባዊ መግለጫዎች (ለምሳሌ በካርቱን፣ በአጫጭር ድራማዎች) ለሕዝቡ ማሳየት። የኢትዮጵያን የባሕር በር ጥያቄ ለጎረቤት ሀገራትና ለዓለም ስጋት ሳይሆን ለጋራ ብልጽግና መሆኑን የሚያሳዩ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላቸው የጥበብ ስራዎችን ማዘጋጀት እንደሚቻልም የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ፕ) ይገልጻሉ።

ነብዩ (ረ/ፕ) ኪነ ጥበብን የሚያዩት እንደ መዝናኛ ብቻ ሳይሆን የሀገር ግንባታ ዋነኛ ምሰሶ አድርገው ነው። እርሳቸው እንደገለጹት፣ አንድ ሀገር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሰሚነት የሚወሰነው በወታደራዊ ኃይል ብቻ ሳይሆን በባህሏና በኪነ ጥበቧ ነው። ኪነ ጥበብ የሀገርን መልካም ገጽታ በመገንባት፣ የውጭ ሀገራትን ልብ በማሸነፍና ብሔራዊ ጥቅምን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለማስከበር ትልቁ መሣሪያ እንደሆነ ይከራከራሉ።

ሙያተኞቹ ስለ ባሕር በር አስፈላጊነት ሲቀሰቅሱ በደረቅ ፖለቲካዊ ንግግር ሳይሆን፣ በሰው ልጅ ስሜትና ፍላጎት ላይ ተመስርተው መሆን አለበት። ለምሳሌ፣ አንዲት እናት ልጇን የምታሳድግበት ወጪ ከወደብ ኪራይ ጋር ያለውን ትስስር የሚያሳይ ታሪክ ትልቅ ተፅዕኖ አለው። የዘመኑ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች አሏቸው። እነዚህን ተከታዮች ለሀገር ጥቅም ማሰለፍ፣ የሀሰት ትረካዎችን መመከትና የሀገራቸውን እውነት ለዓለም ማስተዋወቅ ይኖርባቸዋል።

የጥበብ ሰዎች ከታሪክ ተመራማሪዎችና ከጂኦ-ፖለቲካ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት እውነተኛ መረጃን መነሻ ያደረጉ ስራዎችን ማምረት ይኖርባቸዋል። መንግስትና የግል ባለሀብቶች በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ ለሚሰሩ የኪነ ጥበብ ስራዎች ልዩ ድጋፍና ፈንድ ማመቻቸት፣ የኢትዮጵያን ነባራዊ እውነት የሚያሳዩ ስራዎችን በዓለም አቀፍ መድረኮች እንዲቀርቡ ስልታዊ ድጋፍ ማድረግ ይገባል የሚለውም የባለሙያዎች አስተያየት ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም የሚከበረው ዜጎቿ ስለ ጥቅማቸው በሚገባ ሲረዱና በአንድ ድምፅ ሲቆሙ ነው። ኪነ ጥበብ ደግሞ ልብንና አዕምሮን የማገናኘት ተዓምራዊ አቅም አለው። የባሕር በር ጥያቄውም የፍትሕና የልማት ጥያቄ መሆኑን ዓለም እንዲረዳው፣ ኢትዮጵያዊውም በባለቤትነት እንዲቆምለት የኪነ ጥበብ ሰዎች እንደ ቀደሙት አባቶቻቸው በብዕራቸውና በዜማቸው ግንባር ቀደም ሆነው ሊሰለፉ ይገባል።

የፊልም ኢንዱስትሪን በአግባቡ አለመጠቀም በሀገር ገፅታ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ያሳሰቡት ነብዩ (ረ/ፕ) የዘርፉ ባለሙያዎች ዘርፉን ለማሳደግ በኃላፊነት ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። ሙዚቃዎቻችን፣ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ጌጣጌጦች፣ የቁንጅና ውድድሮችንና መሰል የጥበብ ስራዎችም ሚናቸው ከፍተኛ ስለመሆኑም ሊዘነጋ አይገባም ሲሉ አክለዋል፡፡

ልክ እንደ ማዕድናት ሀብት ሁሉ ጥበብና ባህልም ለአንድ ሀገር ሀብት ናቸው የሚሉት ነብዩ (ረ/ፕ) “የአንድ ሀገር ጥንካሬ የሚለካው በወታደራዊ ብዛት ወይም በኒውክሌር ቴክኖሎጂ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የሀገሪቱን ታሪክ፣ ስልጣኔና ማንነት በፈጠራ ሥራዎች ለዓለም ማሳወቅ የዘመናዊው ዲፕሎማሲ ዋነኛ መሣሪያ ነው” ብለዋል።

አንድ ሀገር የገጠሟትን ፈተናዎች በድል ለመሻገር የዜጎች አንድነት ወሳኝ ነው። ሙዚቃ ልዩነትን አጥብቦ የጋራ ስሜት የመፍጠር ጉልበት አለው። በጦርነት ወቅት ወታደሩን የሚያበረታቱ ቀረርቶዎችና ፉከራዎች፣ በሰላም ጊዜ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን የሚያወድሱ ዜማዎች የዜጎችን ስነ-ልቦና ይገነባሉ። የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ስለ ሀገራቸው ታላቅነት፣ ታሪክና እሴት ካላዜሙ፣ ካልጻፉና ካልተወኑ፣ የውጭ ኃይሎች እንደፈለጉ አድርገው ይተርኩታል። ይህ ደግሞ ብሔራዊ ጥቅምን ይጎዳል። ስለዚህ ኪነ ጥበብ የሀገርን እውነተኛ መልክ ለዓለም በማሳየትና ዜጎችንም ለጋራ ዓላማ በማሰባሰብ  ብሔራዊ ጥቅምን እንደሚያረጋግጥ ድምጻዊ መምህሩ ይናገራል።

የኪነ ጥበብን ጉልበት ይበልጥ ያሳይልን ዘንድ አንዳንድ የጥበብ ስራዎችንና ሀገራትን ተሞክሮ በማሳያነት ጠቅሰን ጽሑፋችንን እንቋጭ፡፡ ሆሊውድ ያመረተው ሌላኛው ብላክ ሃውክ ዳውን (Black Hawk Down) ፊልም እንደ ‘ቶፕ ገን’ ሁሉ ብሔራዊ ጥቅም በማስጠበቁ ረገድ የተጫወተው ኃላፊነት ቀላል አልነበረም፡፡ ፊልሙ አሜሪካ በሌሎች ሀገራት ጣልቃ የምትገባው ለሰብአዊ መብት መከበርና ለዴሞክራሲ ግንባታ እንደሆነ የሚያሳይ ትርክት በመፍጠር፣ ለዲፕሎማሲያዊ ሥራዎቿ መንገድ ጠርገዋል።

ደቡብ ኮሪያ እንደዚሁ ‘Hallyu’ (Korean Wave) በተሰኘው እንቅስቃሴ የፊልም እና የሙዚቃ ኢንዱስትሪዋን በመጠቀም በዓለም ላይ ያላትን ተቀባይነት ቀይራለች። ፓራሳይት እና ስኩዊድ ጌም የተሰኙ የፊልም ስራዎች የኮሪያን ቋንቋ፣ ምግብና ፋሽን ዓለም እንዲያውቀው በማድረግ ለንግድ ሥርዓቷ ጭምር ትልቅ በር ከፍተዋል።

ሎርድ ኦፍ ዘሪንድ (The Lord of the Rings) የተሰኘው ፊልም በኒውዚላንድ ከተቀረጸ በኋላ፣ ወደ ሀገሪቱ የሚገቡ ቱሪስቶች ቁጥር በየዓመቱ በ50 በመቶ አድጓል። ይህም ለኒውዚላንድ ኢኮኖሚ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር አስገኝቷል የሚለውም መረጃ ሌላኛው ነው።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review