አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል

You are currently viewing አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል

AMN- ጥር 16/2018 ዓ. ም

አዲስ አበባን የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ ከኤ ኤም ኤን ጋረ ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ እምብርት የሆነችው አዲስ አበባ አዲስና ዘመናዊ መልክ እየያዘች መሆኗን ከተማዋ ስሟንና ግብሯን ለማመጣጠን በምታደርገው ጥረት የውጭ አገር ዜጎችን ጭምር እየሳበች መሆኑን የቢሮ ኃላፊው ጨምረው ተናግረዋል፡፡

በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር እና የማስዋብ ስራዎች ለነዋሪዎቿ ምቹ ከመሆናቸው ባለፈ፣ የቱሪዝም መዳረሻነቷን እያረጋገጡ እንደሚገኙ አንስተዋል፡፡

ዜጎች ፅዱና ለመኖሪያ ምቹ የሆነ ከተማ ያሻቸዋል የሚሉት ኃላፊው፣ ባለፉት ዓመታት በተሰራው ስራም ይህንን ግብ እውን ከማድረግ አልፎ መዲናዋን የኮንፍረንስ ቱሪዝም መናገሻ ማድረግ ስለመቻሉ ገልፀዋል።

በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ነዋሪዎች የነበራቸውን የስራ ባህል እንዲቀይሩ ማድረጉን ጠቁመዋል።

በዚህም ዜጎች በምሽት ተጨማሪ ስራዎችን የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል ብለዋል።

በመዲናዋ የሚከናወኑ የውበትና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የህዝቡን ተጠቃሚነት ማዕከል ያደረጉ በመሆናቸው ተጠናክረው ይቀጥላሉ ያሉት ኃላፊው በቀጣይ ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤም ለሌሎች ሃገራት ተሞክሮን የሚሰጥ ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በከተማዋ በተሰሩ ስራዎች ለአጭር ጊዜ ሁነት ብቻ ሳይሆን በቀጣይ በሃገራችን ለሚከናወኑ ሁነቶችም ጭምር ታሳቢ ተደርገው እየተሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የመዲናዋን ሰላሳ በመቶ አካባቢ በአረንጓዴ ልማት በመሸፈን ደረጃዋን ለማሳደግ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን ሃያ ሁለት በመቶውን የከተማዋን ክፍል በአረንጓዴ ልማት መሸፈን ስለመቻሉም አስታውሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስራ አጋጣሚ እና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ አዲስ አበባ የሚመጣ የትኛውም የውጭ አገር ዜጋ ስለ አዲስ አበባ በጎ ጎን መመስከር እየተለመደ መጥቷልም ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review