AMN- ጥር 20/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ስድስት ወራት በሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩ ውስጥ 9 ሺህ የሚሆኑት ወደ ሕጋዊ አሠራር ገብተዋል ሲል የአዳስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለፀ።
በመዲናዋ መደበኛ ያልሆነ ንግድን ሥርዓት ለማስያዝ የሚያስችል ደንብ ቁጥር 184/17 ፀድቆ ወደ ሥራ ከገባ ስድስት ወራት ተቆጥሯል።
አፈፃፅሙን አስመልክቶ ከኤ.ኤም.ኤን ሃያ አራት ሰባት ዜና ጋር ቆይታ ያደረጉት የቢሮው የንግድ ግብይትና የገበያ ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ ፀጋዬ ደበሌ፣ 11 ሺ 112 ነጋዴዎች ወደ ሥራ ለማስገባት መለየታቸውን ገልፀዋል።
ከተማዋ ውስጥ ሕገወጥ የጎዳና ላይ ንግድ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ ደንቡ መውጣቱንም አንስተዋል።
ቀደም ሲል የነበረው ደንብ የጊዜ ገደብ እና የካፒታል መጠን ያስቀመጠ ባለመሆኑ ማሻሻል እንዳስፈለገውም ነው የገለጹት።
አሁን ተግባራዊ የተደረገው ደንብ ሁለት ዓመት የጊዜ ገደብንና የካፒታል መጠናቸውም ከሁለት መቶ ሺህ ብር በታች መሆን እንዳለበት በግልፅ የሚያስቀምጥ መሆኑን አቶ ፀጋዬ ተናግረዋል።
9 ሺዎቹ ነጋዴዎች በአምስት ዘርፎች ተመዝግበው ወደ ሥራ መግባታቸውንም ነው የጠቀሱት።
የደንቡ መተግበር የጎዳና ንግድ በከተማዋ ፅዳት፣ ትራፊክ እንቅስቃሴ እና ፀጥታ ላይ ይፈጥራቸው የነበሩ ችግሮችን ማስቀረቱንም አቶ ፀጋዬ ደበሌ ገልፀዋል።
ነጋዴዎችም በተረጋጋ ሁኔታ መሥራት የሚችሉበት ዕድል እንደተፈጠረላቸው ነው የተናገሩት።
ወደ ሥራ እንዲገቡ የተደረጉት ነጋዴዎች በተሰጣቸው ቦታ ላይ እስከ ሁለት ዓመታት የሚሥሩ ሲሆን፣ ቀድመው ካፒታል የሚፈጥሩ ከሆነም ባጠረ ጊዜ ወደ መደበኛ ንግድ እንዲሸጋገሩ ይደረጋል ብለዋል።
በታደሰ ሽፈራው