AMN የካቲት 03 ቀን 2018 ዓ.ም
በ2022 እና 2025 በወጣው ሪፖርት በአምስቱ የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ውስጥ ያሉ ጥቁር አሰልጣኞች ቁጥር እጅግ ጥቂት መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በተለይ በስፔን ላሊጋ አንድም ጥቁር አሰልጣኝ አለመኖሩ ነገሩ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጓል፡፡
ሰሞኑን በተካሄደው የአፍሪካ ዋንጫ የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድንን ይዘው ሦስተኛ ደረጃን ያገኙት ኤሪክ ቺሌ ‹‹ማድሪድን የማሰልጠን እቅድ አለኝ›› ማለታቸው እየተከበረ ባለው የጥቁሮች ወር አጀንዳ ሆኗል፡፡
ኮትዲቯር መዲና አቢጃን የተወለዱትና ለቤተሰቦቻቸው ሀገር ማሊ ብሄራዊ ቡድን የተጫወቱት ቺሌ፤ በፈረንሳዩ ሌንስን ጨምሮ በተለያዩ ክለቦች በመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫውተው አሳልፈዋል፡፡ ጫማቸውን ከሰቀሉም በኋላ የማሊ ብሄራዊ ቡድንን እና በርካታ ክለቦችን በዋና አሰልጣኝኘት መርተዋል፡፡

የናይጄሪያ ብሄራዊ ቡድን የወቅቱ አሰልጣኝ ቺሌ ፤ ከአር ኤም ሲ ስፖርት ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ሪያል ማድሪድን የማሰልጠን ህልም እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የ48 ዓመቱ ቺሌ ‹‹የአፍሪካ አሰልጣኞች እድል ካገኙ ውጤታማ መሆን ይችላሉ ፣ አፍሪካውያን እንደ ማድሪድ ያለ ታላቅ ክለብን የመምራት አቅም አላቸው›› ብለዋል፡፡
ኤሪክ ቺሌ የማድሪድን የማሰልጠን እቅድ እንዳላቸው ቢናገሩም የስፔን ላሊጋ ታሪክ ግን በተቃራኒው ነው፡፡ የስፔን ላሊጋ ለጥቁር አሰልጣኞች በሩ ዝግ ነው፡፡ እኤአ በ2004/05 ቫሌንሲያን ያሰለጠኑት ፈረንሳዊው አንቶን ኮምባውሬ የላሊጋው ብቸኛው ጥቁር አሰልጣኝ ናቸው፡፡ ይህ ነገ ወደ ማድሪድ ሲሄድ ደግሞ ከዚህም የባሰ ነው፡፡ ሎስ ብላንኮዎቹ አንድም አፍሪካዊ አሰልጣኝ ቀጥረው አያውቁም፡፡

ማድሪድ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫን 15 ጊዜ አንስቷል፡፡ 36 የላሊጋ ዋንጫዎችን ጨምሮ ለቁጥር የሚያዳግቱ ስኬቶችን አስመዝግቧል፡፡ ለአሰልጣኝ ቅጥር እጅግ የሚጠነቀቀው እንደ ሁዋንዴ ራሞስ፣ ጆዜ ሞሪንሆ፣ ካርሎ አንቸሎቲ፣ ራፋኤል ቤኒቴዝ፣ ዚነዲን ዚዳንን ቀጥሮ ከማሰናበት ላልታቀበው፣ በቅርቡም በስንት ድርድር ያመጣውን ዣቪ አሎንሶ አሰናብቶ የቀድሞ ተጨዋቹን አልቫሮ አርቤኦላን በጊዜያዊ ኃላፊነት የቀጠረው ማድሪድን ወንበር መረከብ የቺሌ እቅድ መሆኑ አነጋግሯል፡፡
ለማሊ ብሄራዊ ቡድን አምስት ጨዋታዎችን ብቻ ያደረጉት ቺሌ የዋና ከተማዋ ክለብ የቅጥር ማስታወቂያ ሲያወጣ ከሚወዳደሩት መካከል አንዱ እንደሚሆኑ መግለጻቸው ለጥቁሮች ተስፋ ፈንጥቋል፡፡
እንደ ስፔን ባይሆንም እንግሊዝም ከዚህ የተለየ ታሪክ የላትም፡፡ የቼልሲ የቀድሞ አሰልጣኝ ሩድ ጉሌት፣ የኪዊንስ ፓርክ ሬንጀርስ የቀድሞ አለቃ ዚሚ ፍሎይድ ሃሰልባንክ፣ የብላክበርንሮቨርስ የቀድሞ አሰልጣኝ ፖል ኢንስ፣ የፓላሱ ፓትሪክ ቪየራ እንዲሁም የብራይተኑ ክሪስ ሁተን በፕሪምየር ሊጉ የማሰልጠን እድል ካገኙ ጥቁር አሰልጣኞች መካከል የሚታወሱ ናቸው፡፡
በታምራት አበራ