AMN – የካቲት 11/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ያስተናገደቻቸው 39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ እና ሁለተኛው የጣሊያን-አፍሪካ ጉባኤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም አቅሟ ከፍ እንዲል ያስቻሉ መሆኑን የሕግ ምሁርና የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ተንታኝ አቶ ማሩ አብዲ ገለጹ።
አቶ ማሩ አብዲ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ሰሞኑን የተካሄዱት ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች የኢትዮጵያን የቱሪዝም ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩና የሀገሪቱን ዲፕሎማሲያዊ ተጽዕኖ ከፍ ያደረጉ መሆናቸውን ነው።
ኢትዮጵያ በእነዚህ መድረኮች ያሳየችው ዝግጅት አዲስ አበባ ከተማ የአፍሪካ መዲና ብቻ ሳትሆን የዓለምም ቁልፍ መድረክ መሆኗን ዳግም ያረጋገጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

እንደ አቶ ማሩ ገለጻ፣ የሀገራት መሪዎች የተለመዱ ዲፕሎማሲያዊ ፕሮቶኮሎችን በመተው የከተማዋን ሙዚቃና ድባብ እየተጋሩ እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸው መደረጉ ለኢትዮጵያ የገጽታ ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ ነበረው።
ይህም ኢትዮጵያ በቱሪዝም ዘርፍ እያሳየች ያለችውን እድገት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ምቹ አጋጣሚ የፈጠረ ሲሆን፣ መሪዎቹ የኢትዮጵያን አንድነትና የጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱ አስችሏቸዋል ብለዋል።
በተለይም የኢትዮጵያ ወቅታዊ ጥያቄ የሆነው የቀይ ባሕር ጉዳይ ለመሪዎቹ ቀርቦ ግንዛቤ የተወሰደበትና አዎንታዊ ምላሽ የተገኘበት መድረክ መሆኑ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር የጎላ ሚና እንደነበረውም አቶ ማሩ አብራርተዋል።
በበረከት ጌታቸው