ኢትዮጵያ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በሰራችው ሥራ እውቅና አገኘች

ኢትዮጵያ ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለመከላከል በሰራችው ውጤታማ ሥራ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሥነ ሕዝብ ድርጅት እውቅና ማግኘቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር ) በትናንትናው እለት በኒውዮርክ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው ሽልማቱን መቀበላቸው ተገልጿል፡፡

ሚኒስትሯ የኢትዮጵያ መንግስት በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማስወገድ የወሰዳቸውን የህግ፣ የፖሊሲና የፕሮግራም እርምጃዎች አብራርተው እውቅናና ሽልማቱ መንግስት ለስርዓተ ፆታ እኩልነትና ሴቶችን ለማብቃት ያለውን ቁርጠኝነት የበለጠ የሚያጠናክር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምክትል ዋና ፀሐፊ አሚና መሀመድ ፣ የተባበሩት መንግስታት ስነ ህዝብ ድርጅት (UNFPA) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ናታኒያ ካኔምና ሌሎች የተ.መ.ድ አባል ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሥራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ያለ እድሜ ጋብቻና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስወገድ የተቋቋመው ጥምረት እ.ኤ.አ በ2012 የተመሰረተ ሲሆን በጥምረቱ ውስጥ የመንግስት ተቋማት፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅቶች፣ የምርምር ተቋማትና የሀይማኖት ተቋማት እንደሚገኙ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review