AMN- መጋቢት 10/2018 ዓ.ም
በመካከለኛው ምስራቅ የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ የተፈጠረውን የነዳጅ ዋጋ ንረት ለመቋቋም መንግስት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ሲሆን፤ ከእርምጃዎች መካከል የነዳጅ ድጎማ እና ህገ-ወጥ የነዳጅ ግብይትን መቆጣጠር ይገኝበታል፡፡
ይህንን ተፅዕኖ ለመቋቋም የኢትዮጵያ መንግሥት በነዳጅ ምርቶች ላይ የሚያደርገውን የድጎማ መጠን አሳድጓል።
በዚህም መሠረት በዓለም ገበያ አንድ ሊትር ነጭ ናፍጣ 238 ብር ከ13 ሳንቲም እየተሸጠ ቢሆንም፣ መንግሥት ለአንድ ሊትር 98 ብር ከ33 ሳንቲም ድጎማ በማድረግ ለህዝብ በ139 ብር ከ84 ሳንቲም እንዲቀርብ እያደረገ ይገኛል።
ይህም ቀደም ሲል ከነበረው የ53 ብር ከ68 ሳንቲም የድጎማ መጠን ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም ገበያ 205 ብር ከ74 ሳንቲም የሚሸጠው አንድ ሊትር ቤንዚን፣ መንግሥት የድጎማ መጠኑን በ155 በመቶ በማሳደግ በሊትር 73 ብር ከ56 ሳንቲም እየደጎመ ይገኛል።
በዚህም ምክንያት ቤንዚን ለህብረተሰቡ በሊትር 132 ብር ከ18 ሳንቲም እየቀረበ መሆኑ ታውቋል።
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት፣ የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር አዳዲስ የነዳጅ ማከማቻዎች በፍጥነት ወደ ገበያ እንዲገቡና በመጠባበቂያነት ተይዞ የነበረው ነዳጅ ለስርጭት እንዲውል እየተደረገ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ ከስርጭት ሰንሰለቱ ውጭ ነዳጅን በጥቁር ገበያ በሚያዘዋውሩና በህገ-ወጥ ተግባር ላይ በሚሳተፉ አካላት ላይ መንግሥት ጥብቅ የቁጥጥርና የህግ እርምጃዎችን እንደሚወስድ መግለፃቸው ይታወቃል ።
ባለፉት ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ታዲያ በመካከለኛው ምሥራቅ በተፈጠረው ቀውስ የተነሣ ነዳጅ ገዝተው የሚጠቀሙ ሀገሮች እንደልብ ለማግኘት ተቸግረዋል በመሆኑም ችግሩ ተፈትቶ ወደ መደበኛው የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓት እስክንመለስ ድረስ ነዳጅን በቁጠባና ለመሠረታዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት መጠቀም ይኖርብናል። ሲሉ መልእክት ማስተላለፋቸው ይታወቃል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤም የከተማዋ ነዋሪዎችም አጫጭር መንገዶችን ፣በእግር በመጓዝ፣ እንዲሁም የብስክሌት አማራጮችን እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን እንዲጠቀም ጥሪ አቅረበዋል ።
መንግሥት በየዓመቱ ከ4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በጀት በመመደብ ከ4 ነጥብ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ ነዳጅ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚያስገባ መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡
በበረከት ጌታቸው