“በልጅነቴ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እወድዳለሁ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ይህን የምከውነው ደግሞ ወደ ጫካ በመሄድ ነበር። በዚህ አካባቢ የሚገኙ ረዣዥምና አረንጓዴ የሆኑ ተክሎችን መመልከት በማዘውተሬ ለአረንጓዴ ስፍራ ልዩ ፍላጎት አደረብኝ፡፡ ንፁህ እና አረንጓዴ ስፍራ ሀሴትን ይፈጥርልኛል። በከተማዋ ባሉ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ መናፈሻዎች በመሄድ ልጆቼን ይዤ መዝናናትም ያስደስተኛል” ይላሉ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 በተለምዶ ሸጎሌ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ የሚኖሩት አቶ ኑረዲን ዲልሰቦ፡፡
ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ኑረዲን መርካቶ አካባቢ በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሲሆን በአካባቢያቸው ደግሞ በአረንጓዴ ልማት ስራ ይታወቃሉ። በለጋነት እድሜያቸው ከአረንጓዴ ተክሎች ጋር የነበራቸው ቁርኝት ጎልብቶ በአሁኑ ወቅት መኖሪያ አካባቢያቸውን አረንጓዴ የማድረግ ፍላጎቱ አደረባቸውና ተገበሩት፡፡
አቶ ኑረዲን ቀድሞም ያልሙትና ይመኙት የነበረውን የመኖሪያ ቤታቸውን ግቢና ፊት ለፊት ያለውን ስፍራ አረንጓዴ አለበሱት። ወረዳው ከቤታቸው ፊት ለፊት ያለውን ቦታ የአረንጓዴ ስፍራ (Green Area) እንዲያደርጉት በፈቀደው መሰረት ነው የዛሬ አምስት አመት ማልማት የጀመሩት፡፡

አቶኑረዲንዲልሰቦ በመኖሪያአካባቢያቸውያለሙትን አረንጓዴ ስፍራ ሲንከባከቡ
ይህ ስፍራ ፅዱና አረንጓዴ ከመሆኑ አስቀድሞ የነበረውን ገፅታ አቶ ኑረዲን ሲገልፁ፤ “እኔ ይህን ስፍራ ከማልማቴ አስቀድሞ ቆሻሻ ይጣልበት ነበር፡፡ ቦታውን አፅድቼ አረንጓዴ ተክሎችን እና የተለያየ የአበባ ዝርያ እንዲሁም ፅድ ተክያለሁ፡፡ በዚህ መንገድ ንፁህ አካባቢ መፈጠሩ የመንፈስ እርካታ ሰጥቶኛል” ብለዋል አቶ ኑረዲን፡፡
ከመደበኛ ስራቸው ጎን ለጎን ለአትክልቶቻቸው ከፍተኛ እንክብካቤ የማድረግ ስራም ይከውናሉ፡፡ ከልጆቻቸው ጋር በመሆን አበቦችን መኮትኮት፣ ውሃ ማጠጣት፣ ያደገውን አትክልት ማስተካከል የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ በመኖሪያ አካባቢያቸው ቆሻሻ በየመንገድ እንደማይጣል፣ ለዚህ በተዘጋጀው ቦታ ብቻ እንደሚጣል ነው ያጫወቱን፡፡ ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር መልካም ተግባር እንደሆነም ለመገንዘብ ችለናል፡፡
የሳቸውን ተሞክሮ በመውሰድም ሌሎች ግለሰቦች በመኖሪያ አካባቢያቸው አረንጓዴ ተክሎችን እየተከሉ ይገኛሉ፡፡ “አንዳንድ ግለሰቦች ከሌላ ቦታ መጥተው እንዴት እንዳለማሁ ይጠይቁኛል፤ በፎቶ አንስተውም ይሄዳሉ” ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አቶ ኑረዲን ከአረንጓዴ ልማቱ ባለፈ ንፅህና የማይደራደሩበት ጉዳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ “ንፁህ ነገር በጣም እወዳለሁ። ከቤቴ ባለፈ ማንኛውም ቦታ ብሄድ፤ በአካባቢዬም ቆሻሻ ካየሁ አላልፍም፤ አፀዳለሁ። ከወረቀት ጀምሮ የትም ቦታ አልጥልም፡፡ ወይ ቆሻሻ መጣያ አለበለዚያ ቤቴ ወስጄ ቆሻሻ ማስቀመጫ ቅርጫት ውስጥ ነው የምጥለው፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች በአካባቢያችን ሲያልፉ አረንጓዴ ቦታ ሆኖ እያዩ ያልተገባ ተግባር የሚያከናውኑ እንዲሁም ቆሻሻ የሚጥሉ ያጋጥማሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በሚመለከተው አካል ቢሰራ መልካም ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት በአረንጓዴ ልማቱ እያደረገ ያለው ተግባር የሚደገፍና መልካም ተግባር ነው የሚሉት አቶ ኑረዲን፣ በአዲስ አበባ በየአካባቢው ቆሻሻ ሲጣልባቸው የነበሩ ቦታዎች አሁን ንፁህና አረንጓዴ እየሆኑ ይገኛሉ። ሳቢና ንፅህናው የተጠበቀ አካባቢ እንዲፈጠር አድርጓል፡፡ ይህ የአረንጓዴ ልማቱ ትሩፋት ነው ብለዋል፡፡
“በአረንጓዴ ልማቱ የማደርገውን ተግባር እቀጥላለሁ፡፡ በየጊዜው አትክልቶቼን እንከባከባለሁ፡፡ ሁሉም አካባቢውን ከመኖሪያ ቤቱ በር ጀምሮ ቢያፀዳ፣ መንገድ ላይ ከሶፍትና ወረቀት ጀምሮ የተለያዩ ቆሻሻዎችን ባይጥል፣ አካባቢውን አረንጓዴ ቢያደርግ የአካባቢውን ገፅታ ማራኪና ለኑሮ ምቹ ያደርገዋል፡፡ አዲስ አበባም ፅዱ እንድትሆን የበኩሉን ሚና ይጫወታል” ሲሉም አቶ ኑረዲን ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
አቶ ኑረዲን በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአምስቱም ዙር በችግኝ ተከላ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡ ዘንድሮ በሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ለመሳተፍም ተዘጋጅተዋል። ወረዳውም አካባቢያቸው አረንጓዴና ፅዱ እንዲሆን በየጊዜው የፅዳት ዘመቻ እንዲካሄድ እየሰራ ያለው ስራ የሚበረታታ መሆኑን አክለዋል፡፡
አቶ እስማኤል አባይ ሸጎሌ በሚባለው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ ስለ አቶ ኑረዲን ሲገልፁ፤ “በአካባቢያችን በአረንጓዴ ልማት ተግባራቸው ይታወቃሉ፡፡ ወቅቱን ጠብቀው አረንጓዴ ተክሎችን ውሃ ማጠጣት፣ መኮትኮት፣ ያደጉትን ማስተካከል የዘወትር ተግባራቸው ነው፡፡ አካባቢው ጭቃ፣ ለእይታ የሚከብድ ነበር። እሳቸው ያከናወኑት ተግባር የሰፈሩ ገፅታ እንዲቀየርና በአረንጓዴ ተክሎች ውብ እንዲሆን ከፍተኛ አተዋፅኦ አበርክቷል” ብለዋል፡፡
የአካባቢያችን ነዋሪዎች የእሳቸውን ተሞክሮ በመውሰድ አረንጓዴ ተክሎችን በማልማት ሰፈራችንን ፅዱ አድርገነዋል፡፡ እኔም በመኖሪያ ቤቴ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ አበቦች በመትከል አረንጓዴ አድርጌያለሁ፡፡ የአቶ ኑረዲን ተሞክሮም ጠቅሞኛል” ብለዋል አቶ እስማኤል፡፡
መንግስት የጀመረው የአረንጓዴ ልማት ተግባር ፅዱና ለእይታ የተዋበ አካባቢ እንዲፈጠር እንዲሁም ጤናቸው እንዲጠበቅ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ነው፡፡ አካባቢን ፅዱና አረንጓዴ ለማድረግ ችግኞችን መትከልና መንከባከብ ነው የሚጠበቀው፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ አካባቢውን ፅዱ ቢያደርግ ተጠቃሚ ይሆናል ሲሉ አቶ እስማኤል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
መንግስት በጀመረው የአረንጓዴ ልማት ስራ በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ግለሰቦች በፍላጎታቸው የመኖሪያ አካባቢያቸውን ፅዱና ውብ እያደረጉት ይገኛሉ፡፡ አካባቢን አረንጓዴና ፅዱ የማድረግ ባህሉም እየዳበረ መጥቷል፡፡ አቶ ኑረዲን በራስ ተነሳሽነት ያከናወኑት ተግባር ለሌሎች አርዓያ የሚሆን ነው፡፡
የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ባደረገው ምልከታ አካባቢው በአረንጓዴ ተክሎች የታጀበና ንፁህ የመኖሪያ መንደር ሆኗል። የመናፈሻ ስፍራ ይመስላል፡፡ አረንጓዴና ለአካባቢው ውበት ሆኗል፡፡ ለዓይን በሚማርኩ ውብ አበቦችም ተከብቧል፡፡
በጉለሌ ክፍለ ከተማ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አበባዬ ደምሴ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ፤ ጽህፈት ቤቱ በክፍለ ከተማው አካባቢያቸውን አረንጓዴና ፅዱ ለሚያደርጉ ግለሰቦች ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በክፍለ ከተማው ባለው የችግኝ ጣቢያ የፍራፍሬ፣ የቅመማ ቅመም፣ የውበት፣ የጥላና ሌሎች ተክሎች አሉ፡፡ በአረንጓዴ ልማቱ አካባቢያቸውን ለሚያለሙ ግለሰቦች የሚፈልጉትን ዓይነት ችግኝ በመስጠት ድጋፍ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ፣ በክፍለ ከተማው በአረንጓዴ ልማቱ የተሻለ ከሰሩ ተቋማትና ግለሰቦች ተሞክሮ ሌሎች ልምድ እንዲወስዱ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ በአረንጓዴ ልማቱ አደባባዮችን፣ የመንገድ አካፋዮችን፣ ፓርኮችን የማልማት ስራም እየተሰራ ነው። በዚህም በክፍለ ከተማው በአብዛኛው አረንጓዴና ፅዱ አካባቢ ተፈጥሯል፡፡
አካባቢን አረንጓዴና ፅዱ ማድረግ ከግለሰብ ይጀምራል፡፡ ከውበትና ጥላ ተክሎች በተጨማሪ የምግብ ተክሎችን በመትከል አካባቢን ውብ እንዲሁም ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ኃላፊዋ አክለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ይመኙሻል ታደሰ ለጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መረጃ፤ በመዲናዋ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ ልማት ስራ በግል፣ በማህበር እንዲሁም በጋራ መኖሪያ ቤቶች (በኮንደሚኒየም) አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ከፍተኛ ተሳትፎና እገዛ እያደረጉ ነው፡፡
እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በመኖሪያ አካባቢያቸው ለአረንጓዴ ስፍራ ተለይቶ የተሰጣቸውን ቦታ በጥሩ ሁኔታ እያለሙ፣ አካባቢው ውብና ምቹ መኖሪያ እንዲሆን እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
እንደ ኃላፊዋ ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ አረንጓዴ፣ ውብና ፅዱ እንድትሆን በሚደረገው ጥረት በግለሰብ ደረጃ አካባቢያቸውን አረንጓዴ እያደረጉ ያሉ በርካታ ግለሰቦች ተፈጥረዋል፡፡ ቢሮውም ችግኞችን በሚተክሉበት ወቅት አንዳንድ ዕፅዋት በባህሪያቸው ለሰውም ለእንስሳትም የማይሆኑ ስለሚኖሩ ግለሰቦች በአካባቢያቸው ምን አይነት ተክሎችን መትከል እንዳለባቸው የማማከርና ሙያዊ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ የችግኝ ድጋፍም ይደረግላቸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአረንጓዴ ልማቱ ልዩ ትኩረት በመስጠቱ የለሙ ስፍራዎች አረንጓዴነታቸውን ጠብቀው እንዲዘልቁ፣ ያለሙትም ቦታው ለሌላ አገልግሎት እንዳይውል ካርታ የማውጣ,ት ስራ ተከናውኗል፡፡ በ2015 ዓ.ም ወደ 900 ካርታ ወጥቷል፡፡ በተያዘው በጀት አመት ደግሞ ወደ 359 ካርታ በማውጣት ህብረተሰቡ በይዞታው ያለውን አረንጓዴ ስፍራን የመንከባከብ ስራው ቀጣይነት እንዲኖረው መደረጉን ወ/ሮ ይመኙሻል ገልፀዋል፡፡
ግለሰቦች በደጃፋቸው ያለውን 20 ሜትር ራዲየስ ስፍራ እንዲያለሙ የማልማት ውል ይሰጣቸዋል፡፡ በአረንጓዴ ልማቱ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት ከወረዳ እስከ ክፍለ ከተማ ያለው መዋቅርን ባሳተፈ መልኩ ለ225 አካላት እውቅና በመስጠት የማበረታታ ስራ እየተሰራ መሆኑን የቢሮ ኃላፊዋ ጠቁመዋል።
መዲናዋን አረንጓዴ የማልበስ ጥረት ውጤታማ እንዲሆን በመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከሚደረገው ጥረት ባለፈ የእያንዳንዱ ግለሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነው፡፡ ልክ አቶ ኑረዲን በመኖሪያ ቤታቸው አካባቢ ያለን ትንሽ ቦታ በማልማት ንፅህናው የተጠበቀ፣ አረንጓዴና ለዓይን ሳቢ የሆነ ስፍራ መፍጠር እንደቻሉት ሌሎችም የእንዲህ አይነት ግለሰቦችን ተሞክሮ በመውሰድ ቢተገብሩት አረንጓዴ፣ ፅዱና ለኑሮ ተስማሚ የሆነች ከተማን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የተሳካ ይሆናል እንላለን፡፡
በሰገነት አስማማው