AMN – መስከረም 29/2017 ዓ.ም
የዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት አህጉራዊ ስብሰባ በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን እና በዓለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት አስተባባሪነት በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
በአህጉራችን አፍሪካ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ ባለው ስብሰባ የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ የመንግስት ህግና ፍትህ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ እንደሚገኙበት ተመላክቷል፡፡
እንዲሁም የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የተመድና የሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች፣ የለጋሽ ድርጅቶች ተወካዮች እና የዘርፋ ከፍተኛ ባለሙያዎችም እየተሳተፉበት ይገኛል፡፡
በመርሀ-ግብሩም የፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2018 የጸደቀውን ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነትን በመተግበር ላይ እንደምትገኝ አንስተዋል፡፡

የስምምነቱ አካል ከነበሩት 20 አጀንዳዎች ውስጥ አሥሩን ቅድሚያ በመስጠትና በተለያዩ የልማት ፖሊሲዎችና ዕቅዶች ውስጥ እንዲካተቱና ተፈጻሚ እንዲሆኑ በማድረግ መደበኛ ያልሆነውን ፍልሰት የመከላከልና የመቆጣጠር ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል መደበኛ ፍልሰትን በማስፋት ከፍልሰት የሚገኘውን ጥቅም አሟጦ በመጠቀም ረገድ የተሻሉ አፈጻጸሞችን ማስመዝገብ ችላለች ሲሉም አክለዋል፡፡
በዚሁ መሰረትም በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት አማካኝነት የስምምነቱን ሀገር አቀፍ የአፈጻጸም ሪፖርት በ2020 ለተመድ ያቀረበች ሲሆን፤ በየጊዜው በሚደረጉ የአፈጻጸም ግምገማ መድረኮች ላይም የነቃ ተሳትፎ ስታደርግ እንደቆየች ገልጸዋል፡፡
ይህ ተግባሯም በምስራቅ አፍሪካ የስምምነቱን አተገባበር ውጤታማ በማድረግ ተጠቃሽ እንድትሆን አድርጓቷል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው ዘገባ ያመላክታል፡፡
ኢትዮጵያ የፍልሰት መነሻ፣ መተላለፊያ ብሎም መዳረሻ ሀገር መሆኗን የጠቀሱት ሚኒስትሩ መንግስት ቁርጠኛ አቋም ያለው መሆኑንና ለጉዳዩም ትኩረት በመስጠት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ሀገር አቀፍ የትብብር ጥምረት ካውንስል በማቋቋም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አንስተዋል።
ይህ ዓለም አቀፍ የፍልሰት ስምምነት አህጉር አቀፍ ስብሰባን እንደ መልካም እድል በመጠቀም ተሳታፊዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸውን ልምድ የሚካፈሉበት እንደሚሆንም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል፡፡
ስብሰባው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በፍልሰት ዙሪያ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው ይዳሰሱበታል ተብሎ ይጠበቃል።