በኮሚሽኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ88 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

You are currently viewing በኮሚሽኑ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ከ88 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰብስቧል

AMN- ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም

የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ፤ በኮሚሽኑ በ2017 የበጀት ዓመት በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሰሩ ስራዎችን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል ።

ኮሚሽነር ደበሌ በመግለጫቸው፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት 87.27 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 88.1 ቢሊዮን ብር ወይም የእቅዱን 100.86 በመቶ ማሳካት እንደተቻለ ገልጸዋል።

አፈጻፀሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ38.45 ቢሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱንም ተናግረዋል ።

ኮንትሮባንድን በመከላከል እና በመቆጣጠርም ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውንም ኮሚሽነር ደበሌ ጠቁመዋል፡፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመትም 2.8 ቢሊዮን ብር የገቢ እና 842.8 ሚሊዮን ብር የወጪ በድምሩ ከ3.6 ቢሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለዋል፡፡

ኮሚሽነር ደበሌ አክለውም፤ በንግድ ማጭበርበር እና በኮንትሮባንድ መንግስት ሊያጣው የነበረውን ከ50 . 5 ቢሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከህገ ወጦች ማዳን እንደተቻለም አስረድተዋል።

በህግ ለተፈቀደላቸው የቀረጥ ነጻ ማበረታቻ መብት ተጠቃሚዎችም 34 ቢሊዮን የሚገመት የጉምሩክ አገልግሎት መሰጠቱንም ገልጸዋል: :

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በዋናነት በንግድ ማጭበርበር እና በኮንትሮባንድ ዝውውር ችግሮች ማጋጠማቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ ችግሮቹን ለመፍታት በርካታ እርምጃዎች የተወሰዱ መሆኑንና በቀጣይም በህገወጦች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።

በመጨረሻም ከሚዲያ ባለሙያዎች ለቀረቡ ጥያቄዎች ኮሚሽነር ደበሌ ምላሽ እና ማብራሪያ መስጠታቸውን ከገቢዎች ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review