የጥቅምት 24ቱ ጥቃት ኢትዮጵያ ጠንካራ ሠራዊት እንዳይኖራት እና የምትጠቃ ሀገር እንድትሆን የታሰበ እንደነበር ተገለጸ

You are currently viewing የጥቅምት 24ቱ ጥቃት ኢትዮጵያ ጠንካራ ሠራዊት እንዳይኖራት እና የምትጠቃ ሀገር እንድትሆን የታሰበ እንደነበር ተገለጸ

AMN- ጥቅምት 24/2017 ዓ.ም

የሰሜን ዕዝ በወገኑ የተከዳበት እና የተጨፈጨፈበት 4ኛ ዓመት ዝክረ ሰማዕታት ታስቦ ውሏል፡፡

መርሀግብሩ በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያ ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳንን ጨምሮ ጄኔራል መኮንኖችና የሠራዊት አባላት በተገኙበት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ታስቦ ውሏል።

የመከላከያ ሠራዊት የሥነ-ልቦና ግንባታ ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው ወልደኪዳን 4ኛ ዓመት ዝክረ-ሰሜን ዕዝ መታሰቢያ ቀን ለመላው ሠራዊቱ ፅናትና ሀገር የማስቀደም እሴታችን በተግባር ያረጋገጥንበት በመሆኑ ፤ለህዝባችን በከፈልነው ዋጋና ባሳየነው ፅናት ፣ጀግንነት እና ጥልቅ የሆነ የሀገር ፍቅር ልንኮራ ይገባል ብለዋል፡፡

ጥቅምት 24 በሠራዊታችን ላይ ዘግናኝና አረመኔያዊ ክህደት ተፈፅሟል ይህ ድርጊት ኢትዮጵያ ጠንካራ ሠራዊት እንዳይኖራት እና የምትጠቃ ሀገር እንድትሆን የታሰበ ቢሆንም ሠራዊቱ እጅ አንሰጥም ሀገራችንን አንክድም ቃላችንን አናፈርስም በማለት መስዋዕትነት በመክፈል ሀገር ማስቀጠሉን ጄኔራል መኮንኑ አንስተዋል፡፡

ሠራዊቱ ኢትዮጵያዊያን በክብር እንዲኖሩ ጉልበቱን እና ህያው ነብሱን የሚሰጥ የወገን ቤዛ በመሆኑ በትግራይ ምድርም ዋጋ ከፍሎ የትግራይን ህዝብ ከጥቃት ታድጎ ማህበራዊ ደህንነቱን ጠብቆ የችግርና የስጋት ጊዜን እንዲሻገር አድርጓል ነው ያሉት፡፡

ጥቅምት 24 ድርጊቱ “እንዳይደገም ሁሌም እንዘክረዋልን” ስንል ሠራዊቱ በከሀዲዎች በመጨፍጨፉ ብናዝንም መከላከያ ሠራዊቱ አገራችንን ከመፍረስ በመታደጉ አሁን ላለንበት ደረጃ አብቅቶናል በዚህ ድል እንኮራልን ማለት ነው ያሉት ሜጄር ጄኔራል እንዳልካቸው የጀግኖች አርበኞቻችንን ፅናት ተላብሰን የሀገራችንን እና የህዝባችንን ሠላም ማረጋገጥና ማስቀጠል ይገባናልም ብለዋል፡፡

የመቻል ስፖርት ክለብ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ብርጋዲየር ጄኔራል ኑሩ ሙዘይን በበኩላቸው ሠራዊቱ በወቅቱ ባላሰበበትና ባልገመተው ሁኔታ ቢከዳም ከምንም ተነስቶ ከፍተኛ ተጋድሎ እና መስዋዕትነት በመክፈል ሀገር ማሥቀጠሉን ገልፀዋል።

በጊዜው ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ ከፍተኛ እገዛና ብርታት ሆኖ እንደነበር አዉስተዋል።

የሰሜን ዕዝ በአካባቢው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የሀገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባለፈ ለህብረተሰቡ በብዙ ሺህ የሚቆጠር መስዋዕትነት በመክፈል በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በከሀዲዎች በምላሹ ግን ክህደት እና ግፍ የተሞላበት ግድያ ተበረከተለት ይህ እውነታ በሌሎች ቀጣይ እንዳይደገም ሁሌም ዘብ እንቆማለን ማለታቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review