
AMN-ጥቅምት 25/2017 ዓ.ም
ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ገለፀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ “ግጭትን ማስተዳደር ሰላምን መገንባት “በሚል መሪ ሀሳብ ግጭትን በማስተዳደርና ሰላምን በመገንባት ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ ከ11 ክፍለ ከተማ ለተወጣጡ የወጣቶች ማህበራት አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ እያካሄደ ይገኛል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሚዴቅሳ ከበደ እንደገለጹት፤ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የመዲናዋ ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ የማድረግ ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
ህዝቡን የሰላም ባለቤት በማድረግ ወንጀልን ቀድሞ በመከላከልና የህግ የበላይነትን በማስከበር ረገድ ሰፊ ስራ መሰራቱን አስታውቀዋል፡፡
በመዲናዋ ስድስት ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የንድፈ ሀሳብና የመስክ ስልጠና ወስደው ወደ ሰላም ሰራዊት ገብተው የሰላምና ፀጥታ ስራዎችን እንዲሰሩ ለማድረግ መታቀዱን አመላክተዋል።
ወጣቶች የአካባቢያቸውን ሰላም በማፅናትና በመጠበቅ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ ሚዴቅሳ ጥሪ አቅርበዋል።

የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ ሁኔታ ማስጠበቅ መቻሉን በመጥቀስ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ስራዎች እንዲፋጠኑ የማድረግ ተግባር መከናወኑን ተናግረዋል።
በበጀት አመቱ የመጀመሪያዎቹ ሶሰት ወራት በመዲናዋ የተከበሩ የአደባባይ በዓላት በድምቀት መከናወናቸውን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይ የህዝቡን ተሳትፎና ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የመዲናዋን ሰላምና ፀጥታ ዘላቂና አስተማማኝ በሆነ መልኩ የማፅናት ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው፣ የመዲናዋን ሰላም በመጠበቅና በልማት ስራዎች በመሳተፍ የተጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ እንደሚወጡ ተናግረዋል።
ለወጣቶቹ የሚሰጠው ስልጠና ለተከታታይ ስድስት ቀናት እንደሚቀጥል ተመላክቷል፡፡
በመሀመድኑር ዓሊ