“ግብር ስከፍል የማገኘውን ሰላምና እርካታ በቃላት  መግለፅ አልችልም”

You are currently viewing “ግብር ስከፍል የማገኘውን ሰላምና እርካታ በቃላት  መግለፅ አልችልም”

የሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙስጠፋ ሀጂ አወል

አቶ ሙስጠፋ ሀጂ አወል በ13 ዓመታቸው ነበር ወላጅ እናታቸውን በህይወት ያጡት። በወቅቱ አባታቸው ቡና በመሸጥ በሚያገኙት ገቢ ቢተዳደሩም እሳቸው የቤቱ ታላቅ ልጅ በመሆናቸው ታናናሾቻቸውን የማስተማር እና ቤተሰቡን የማገዝ ኃላፊነት እንዳለባቸው በለጋ እድሜአቸው በመገንዘብ ገቢ የሚያገኙበትን መንገድ አማተሩ፡፡

ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ስምንት ብር ተበድረው ናፍጣ ወደ መቸርቸር ስራ ገቡ። “ጠንክሬ ሰርቼ መለወጥ አለብኝ” በሚልም የጀመሩትን የናፍጣ ችርቻሮ ስራ በማሳደግ ወደተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች ንግድ ስራ ተሰማሩ። በዚህም አልተገደቡም፤ የልጅነት ሩጫና ፈንጠዚያ ሳያምራቸው ታትረው በመስራት በ1960ዎቹ ዓ.ም አጋማሽ “ሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር”ን ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን መሰረቱ፡፡

“ሙለጌ” የእናታቸው ስም ሲሆን ቃሉም የስልጥኛ ቋንቋ ነው፡፡ “ሙለ” የሚለው ቃል ሙሉ ማለት ነው፡፡ “ጌ” ደግሞ ሀገር ማለት ሲሆን ሙለጌ “ሙሉ ሀገር” የሚል ሃሳብ ያዘለ መሆኑን አብራርተውልን ድርጅታቸውን ለእናታቸው መታሰቢያ እንዲሆን “ሙለጌ” ብለው እንደሰየሙት ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

ሙለጌ የቡና ምርትን በሀገር ውስጥ ከማቅረብና ከመሸጥ ባለፈ በ1983 ዓ.ም ወደ ቡና ላኪ ድርጅትነት ተሸጋግሮ በሰፊው እየሠራ ይገኛል፡፡ ቡናን ወደተለያዩ የዓለም ሃገራት ይልካል፡፡ ለአብነት አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ ይልካል፡፡ ከውጭ ደግሞ ብረታ ብረት፣ ኒዶ ወተት፣ መድሃኒትና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን ያስገባል፡፡

ናፍጣ በመቸርቸር የጀመሩት ስራ ዛሬ ላይ ትልቅ ደረጃ ደርሰው የሙለጌ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ለመሆን አብቅቷቸዋል፡፡ ዓመታዊ ገቢውም ወደ 2 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ለ2 ሺህ ዜጎች የሥራ እድል ፈጥረዋል፡፡ አቶ ሙስጠፋ በአሁኑ ወቅትም ከታማኝ ግብር ከፋዮች መካከል አንዱ ለመሆን በቅተዋል፡፡

አቶ ሙስጠፋ ግብርን በታማኝነት፣ ሳይሸራርፉ በወቅቱ የመክፈል ልምድ እንዳላቸው ከጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል፡፡ “ግብርን በወቅቱ የመክፈል ልምድ ያዳበርኩት የንግድ ስራ ከጀመርኩበት ከልጅነት ጊዜዬ ጀምሮ ነው፡፡ የበለጠ ያነሳሳኝ ደግሞ በአንድ ወቅት በደርግ ስርዓት አሜሪካ ሃገር ቴክሳስ ሄጄ ነበር። ጉብኝት በማደርግበት ወቅት ከትምህርት ቤቶች እና ከተገነቡ ዘመናዊ ህንፃዎች ጀምሮ እስከ ትላልቅ የአውሮፕላን፣ የታንክ ፋብሪካና ሌሎችም ሀብቶች የግለሰብ መሆናቸው ተነገረኝ፡፡

በወቅቱ ታዲያ መንግስት ምንድ ነው ያለው? ስላቸው ፖሊስና ፖስታ ቤት ነው አሉኝ፡፡ መንግስት በግብር ነው የሚኖረው። “እዚህ አገር የሰው ነብስ ብታጠፋ እድሜ ልክ ትታሰራለህ፤ ግብር ብታጭበረብር ደግሞ የሞት ፍርድ ይከተላል” አሉኝ፡፡ ሀገሩ በዚህ መልክ ከህዝቡ በሚሰበሰበው ግብር ነው ያደገው አሉኝ። ይህ በአእምሮዬ ተቀርፆ ቀረ፡፡ እንዳየሁት ሀገር ሀገሬም በምታገኘው ግብር እንድታድግልኝ ተመኘሁ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስመለስ ያየሁትን ተሞክሮ ግብር ለሚያስከፍሉ አካላት አጋራሁ፡፡ ይህ አጋጣሚ ቀድሞም ግብር የመክፈል ፍላጎትና ልምድ ስለነበረኝ የበለጠ እንድነሳሳና ግብሬን በወቅቱ እንድከፍል ረድቶኛል” ብለዋል፡፡

“ግብር መንገድ፤ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤት፣ ኤሌክትሪክ በአጠቃላይ ልማት ማለት ነው፡፡ ግብር መክፈል ሰላም ይሰጣል፤ እጅግ በጣም የሚያኮራ ተግባር ነው፡፡ የሚጣልብኝን ግብር  ሁሌም በወቅቱ እከፍላለሁ፡፡ ግብር ስከፍል የማገኘውን ሰላምና እርካታ በቃላት መግለፅ አልችልም፡፡” ይላሉ አቶ ሙስጠፋ፡፡

አቶ ሙስጠፋ ግብርን በወቅቱ ሳይሸራርፉ የመክፈል ጥቅምና ተሞክሯቸውን ከራሳቸው አልፈው ለልጆቻቸው፣ ለቤተሰቦቻቸው፣ በድርጅቱ ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞቻቸውና ለሌሎችም እንደሚያሳውቁና ልጆቻቸውም ግብር የመክፈል ልምድ ማዳበራቸውን ነግረውናል። ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ደረጃ በመድረስ በሚልም የተባበሩት መንግስታት ድርጀትና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ከበርካታ ተቋማት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ የበለፀጉ ሀገራትን ያቀፈው የቡድን 8 (G8) አባል ሀገራት ስብሰባ ላይ ተገኝተውም ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ታማኝ ግብር ከፋይ በመሆንም ለረዥም ዓመታት በተለያዩ ጊዜያት እውቅናና ሽልማት አግኝተዋል።

ከዚህ አልፎ በበጎ ፈቃድ ተግባራት ይሳተፋሉ፡፡ መንገድ፣ ውሃ፣ ትምህርት ቤት፣ ድልድይና ሌሎችም ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሰረተ ልማቶችን በማሰራት እንዲሁም ገበታ ለሀገር ላይ ተሳትፈዋል። በዚህም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበጎ ስራ ላደረጉት ተሳትፎ ሽልማት አበርክቶላቸዋል፡፡

ግብር ለሀገር እድገት የጀርባ አጥንት በመሆኑ ግብርን በወቅቱ መክፈል ይገባል የሚሉት አቶ ሙስጠፋ፤ “ግብር አለመክፈል ራስን መስረቅ፣ ማጭበርበር እንደማለት ነው፡፡ ሰርተን ካተረፍን ለሃገራችን እድገትና ልማት የሚውለውን ግብር መክፈል አለብን። የምንከፍለው ግብር ደግሞ በትክክል የልማት ስራዎች ላይ ከዋለ፣ የጎበጠው መንገድ ከተስተካከለ፣  ውሃ፣ መብራት ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ከተሟሉልንና ተጠቃሚ ከሆንን ግብር ከመክፈል በላይ የሚያስደስት ነገር አይኖርም። ይህን በማድረጋችን የሚሰጠን እውቅናና ሽልማትም ስራችንን የበለጠ እንድንሰራ መነሳሳት ይፈጥርልናል። በመሆኑም ለሀገር ወሳኝ የሆነውን ግብር ሁሉም በወቅቱ መክፈል ይኖርበታል” ሲሉ አቶ ሙስጠፋ ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡   

የግብር ከፋዮች የእውቅናና ሽልማት መርሃ ግብር ‘ግብር ለሀገር ክብር’ በሚል ስያሜ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ ቆይቷል። ዘንድሮ  በተካሄደው  በ6ኛው መርሃ ግብርም በአገር ውስጥ ታክስ እና በወጪ ንግድ ቀረጥና የታክስ አሰራር ስርዓቶችን እና ህጎችን አክብረው ግብር በመክፈል የተሻለ አፈፃፀም የነበራቸው 550 ግብር ከፋዮች የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። የአቶ ሙስጠፋ ድርጅትም በታማኝ ግብር ከፋይነት እውቅና ካገኙት መካከል ሆኗል። በዘንድሮ የግብር መክፈያ ወቅትም እህት ድርጅቶችን ጨምሮ 4 መቶ ሚሊዮን ብር ግብር ከፍለዋል፡፡  በዚህም በወርቅ  ደረጃእውቅና  ተሰጥቷቸዋል፡፡

በወቅቱ እውቅናውን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ “ግብርን በታማኝነት መክፈል የኢትዮጵያን ብልፅግና በራስ አቅም ለማረጋገጥ መሰረት ነው፡፡ በመሆኑም ግብር ከፋዮች ሰርታችሁ፤ ሀብት አፍርታችሁ መልሳችሁ ኢትዮጵያን እየገነባችሁ ስለሆነ ክብር ሊሰማችሁ ይገባል፡፡ መንግስትም ለታማኝ ግብር ከፋዮች ይታመናል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡

እንደ ሀገር ከገቢ ግብር የሚሰበሰበው ገቢ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል፡፡ በ2010 በጀት ዓመት ከገቢ ግብር የተሰበሰበው 170 ቢሊዮን ብር የነበረ ሲሆን፤ በ2016 ዓ.ም 512 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር መድረሱን ከገቢዎች ሚኒስቴር የማህበራዊ ትስስር ገፅ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡ ግብር ለአንድ ሀገር ቁልፍ የልማት መሳሪያ ነው ማለት ይቻላል፡፡ አቶ ሙስጠፋም በግብር ላይ ያላቸው አመለካከትና እያደረጉት ያለው ተግባር ለሌሎች ተምሳሌትና ተሞክሮ የሚሆን ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሌሎች ግብር ከፋዮችም የሳቸውን ዓርአያነት ያለው ተግባር በመከተል፤ ግብርን በወቅቱ በመክፈል የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማፋጠን የድርሻቸውን ቢወጡ መልካም ነው እንላለን፡፡

በሰገነት አስማማው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review