የሰው ልጅ በልምድም ይሁን ቀለም ቆጥሮ ያገኘው የራሴ የሚለው እውቀት ይኖረዋል፡፡ በትምህርቱ ዓለም እስከ ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ በመዝለቅ እውቀት ይገበያል። ፊደል ቆጥሮም ይሁን በልምድ ያገኘውን እውቀት ወደ ስራው ዓለም ሲቀላቀል ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ አንድ ባለሙያ በትምህርት ተቋማት ገብቶ ከሚያገኘው እውቀት ባለፈ በስራ ዓለም በርካታ አዳዲስ ልምምዶችንና እውቀቶችን ይቀስማል፡፡
በስራ ዓለም ያገኛቸውም ሆነ ቀድሞ የሚያውቃቸውን እውቀቶች አሁን ላይ ዘመኑ በሚጠይቃቸው አዳዲስ ነገሮች መቃኘት ስለሚኖርባቸው ስልጠናም ሆነ የልምድ ልውውጥ በማድረግ ይበልጥ እንዲዳብር ማድረግ የግድ ነው፡፡
አንድ ባለሙያ አውቀዋለሁ ብሎ የሚያስበው ማንኛውም ነገር በየጊዜው እሴትን ጨምሮ አዲስ ነገር ይዞ ሊመጣ ስለሚችል በስልጠና ራሱን ማነቃቃትና የበለጠ ለስራ መነሳሳት ይጠበቅበታል፡፡ ሙያዊ ስልጠናዎች የስራ ተነሳሽነትን የሚፈጥሩና ተቋማት የላቀ አፈጻጸም እንዲያስመዘግቡ ጭምር የሚያግዙ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በሚያከናውናቸው የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች በርካታ ሰራተኞችን ይዞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኝ ልማታዊ ተቋም ነው፡፡ ዛሬ ላይ መዲናዋ ለደረሰችበት የመንገድ ልማት ስኬት በባለስልጣኑ ተቀጥረው የሚሰሩ ባለሙያዎች አሻራቸው የላቀ ነው፡፡

በመሆኑም የሰው ሀብት አቅም ግንባታ፤ ሰራተኞች ስራቸውን በውጤታማነት እንዲያከናውኑ በእውቀትና በክህሎት ማነፅና ለእውቀትና መረጃ ተደራሽ እንዲሆኑ ከማስቻል ባሻገር ለሰራተኞች ብሎም ለተቋሙ ምርታማነት ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡
የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስልጠና ማእከል ዳይሬክቶሬት የሰራተኞች አቅም ግንባታ ስራ ላይ ከፍተኛ ትኩረት አድርጎ ይሰራል። የተቋሙ አመራርና ሰራተኞች የእውቀት ክህሎትና የአመለካከት ለውጥ በማምጣት ባለስልጣኑ የተጣለበትን ተቋማዊ ሃላፊነት በብቃት እንዲወጣ የሚያስችሉ በርካታ ሙያዊ ስልጠናዎችን ያዘጋጃል፡፡
አቶ መስፍን ከበረ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስልጠና ማእከል ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው፡፡ የባለሙያ አቅም ግንባታ ስራ በተቋማት ውስጥ ቀዳሚ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባ ያነሳሉ፡፡ ስልጠና አንድ ሰራተኛ በተመደበበት የስራ መስክ ላይ የተሻለ አፈፃፀም እንዲኖረው፣ ስለሚሰራው ስራ በአግባቡ መገንዘብ እንዲችል እና የሚጠበቅበትን ውጤት በብቃት እንዲፈፅም የሚያግዝ ነው። አንድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተመርቆ ወደ ተለያየ የስራ መስክ የሚሰማራ ባለሙያ በትምህርት ዓለም የተገኘው እውቀት እንዳለ ሆኖ በንድፈ ሀሳብ የሚያውቃቸውን ነገሮች በተግባር መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ መስራት ስለሚገባ በስልጠና መታገዝ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ስልጠና በአጭሩ የመማር ወይም የማወቅ ሂደት ነው፡፡ በሥልጠና አዲስና ነባር የባለስልጣኑ ሰራተኞች ያላቸውን ሙያ የሚያሻሽሉበት አጠቃላይ የመፈፀምና የማስፈፀም አቅምን የሚያዳብሩበት አንዱ መንገድ ነው፡፡ ሥልጠና ከመደበኛ ትምህርት የተለየ መሆኑን ያነሱት አቶ መስፍን መደበኛ ትምህርት በአብዛኛው በክፍል ውስጥ በቃላዊ መግለጫዎች ጽንሰ-ሀሳቦችን በማስጨበጥ ወደፊት ከሚጠበቅ ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚሰጥ ሲሆን፤ ሥልጠና ደግሞ የተገኘ ዕውቀትን ወደ ተግባር መለወጥ የሚቻልበት መንገድ ነው፡፡
ስልጠናን በስብሰባ፣በስራ አውደ ጥናት፣በሴሚናሮች፣በአጭርና በረጅም ጊዜ በሚሰጡ የስልጠና መርሀ ግብሮች ማግኘት ይቻላል፡፡ በመሆኑም ሥልጠና በሥራ ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ የዕውቀት፣ የክህሎትና የችሎታ ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያግዝ ዘዴ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ሰራተኞች በተመደቡበት የሥራ መደብ ላይ ብቃት ያላቸው እንዲሆኑና በቀጣይ ሊገጥሟቸው የሚችሉ የሥራ አፈፃፀም ችግሮችን መፍታት ይቻል ዘንድ ሥልጠና በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ መሆኑን ነው አቶ መስፍን የሚናገሩት፡፡
በአጠቃላይ የሰራተኞች አቅም ግንባታ ስራ ሙያን በተሻለ ደረጃ ለማጎልበት፣ እቅድን በአጭር ጊዜ ለማከናወን፣ ያለ አግባብ የሆነ የማቴሪያል ብክነት ለማስቀረት፣ የባህሪ ወይም የአመለካከት ለውጥ በማምጣት የዕለት ከዕለት ሥራ ላይ ውጤታማ ለመሆን፣ ምርታማነትን ለመጨመር፣ ዘመኑ ካስገኛቸው አዳዲስ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ጋር ራስን ለማስተዋወቅና ወቅታዊ መረጃን ለማግኘት እንዲሁም የእርስ በርስ ትውውቅና ልምዶችን በጋራ ለመለዋወጥ የሚያግዝ መሆኑን አቶ መስፍን አያይዘው ተናግረዋል፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚዘጋጁ የስልጠና ይዘቶች በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ የሚሰጡ ተብለው ዓመታዊ እቅድ የሚዘጋጅላቸው ሲሆን፤ ከየስራ ክፍሎች የሚላኩ የስልጠና ፍላጎቶችን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚዘጋጅ ስልጠናም ሌላኛው መንገድ ነው፡፡
በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በውስጥ አቅም መስጠት የሚቻለውን ስልጠና በራሱ ባለሙያዎች የሚሰጥ ሲሆን፤ በትብብርና ክፍያ ተፈፅሞላቸው የሚሰጡ ስልጠናዎች ደግሞ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ይዘጋጃሉ። ባለሙያዎች ስልጠናውን በአካል ተገኝተው ከመሰልጠን ባለፈ ባሉበት ቦታ ሆነው በኦንላይን ስልጠና የሚያገኙበት አግባብ እየተፈጠረ ይገኛል፡፡
እንደ ስልጠናው ይዘት ለሚመለከታቸው የስራ ክፍሎች የስልጠና ፕሮግራም ይላካል። የስልጠና ፕሮግራም የተላከለት ክፍል በተላከለት መረጃ መሰረት የትኛው ባለሙያ ምን አይነት ስልጠና ቢወስድ ሙያዊ አቅሙን ያጎለብታል የሚለውን በመለየት ባለሙያዎችን ለስልጠና ይልካል፡፡

በዚህም መሰረት ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በ2017 በጀት ዓመት ለበርካታ ሰራተኞች ሰልጠና እና የትምህርት እድልን ለማመቻቸት እቅድ የያዘ ሲሆን፤ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ 644 የሚሆኑ ባለሙያዎች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
የስልጠናዎቹ ይዘት
የአጭር ጊዜ ስልጠና
ከአንድ ቀን ጀምሮ እስከ ሶስት ወራት ባሉት ጊዜያት የሚሰጥ ማንኛውም ሙያዊ ስልጠናን ያካትታል፡፡ አሁን ላይ ባለስልጣኑ በዚህ የስልጠና እቅድ ውስጥ አብዛኛውን ሰራተኛ ተሳታፊ እያደረገ የሚገኝበት አግባብ ነው ያለው። በዚህ የስልጠና መርሀ ግብር ውስጥ Digital Communication፣ Construction Contract Administration፣ Construction Materials Management፣ Construction Law፣ Basic of Construction Project Management፣ Contract Planning & Procurement Management፣ Leadership and Construction Company Management፣ Construction Financial Management፣ Construction Project Human Resource Management፣ Primavera Project planner ስልጠና ከተሰጡባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የመካከለኛ ጊዜ ስልጠና
ከሶስት ወራት ላላነሰ ይኸውም ከአንድ ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ቆይታ የሚሰጥ ማንኛውም የውጪም ሆነ የሀገር ውስጥ ስልጠናን የያዘ ነው፡፡
የረጅም ጊዜ ስልጠና
ባለሙያዎች አንድ ዓመትና ከዚያ በላይ በሚቆይ ጊዜ ውጪ ሀገር ሄደውም ሆነ ሀገር ውስጥ ሆነው ስልጠና የሚያገኙበት አግባብ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እስከ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ያሉ የተለያዩ ደረጃዎችን የሚያካትት ሲሆን፤ ከህብረት ስምምነቱ፣ ከትምህርትና ስልጠና መመሪያ ጋር በተገናዘበ መልኩ ከተቋሙ ፍላጎትና ጠቀሜታ አንፃር ተገምግሞ በውድድር የሚከናወን ነው፡፡
በተቋሙ በኩል ሰራተኞች የረጅም ጊዜ ስልጠናም ሆነ የትምህርት እድሎችን እንዲያገኙ ከማመቻቸት ጋር በተያያዘ ሰፊ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በዚህም በ2017 በጀት ዓመት 35 ለሚሆኑ አመራሮችና ሰራተኞች የሀገር ውስጥ የትምህርት እድል ለማመቻቸት እቅድ ተይዟል።
የትምህርት ዝግጅቱ በሁለተኛ ዲግሪ፣ በመጀመሪያ ዲግሪ እና በዲፕሎማ ደረጃ የሚሰጥ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ ከተለያዩ የውጭ ሀገራት በሚገኙ የትምህርት እድሎች አመራር እና ሰራተኞችን ለማሳተፍ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡
ከዚህ ቀደም በተሰጡ የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎች በተቋሙ የስራ ጥራት እና ቅልጥፍና ከማሳደግ፣ ስራን በእቅድ ከመምራት እና መረጃ አያያዝን ከማዘመን አንፃር አይነተኛ ለውጥ ማምጣት ተችሏል፡፡
በሐመልማል ከበደ (ከአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን)