ኢትዮጵያ በምርታማነት ላይ ያስመዘገበችው ስኬት ከረሃብ ነፃ አህጉር መፍጠር እንደሚቻል አመላካች ነው – ገርድ ሙለር

AMN-ጥቅምት 26/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በምግብ ምርታማነት ላይ ያስመዘገበችው ስኬት ከረሃብ ነፃ አህጉር መፍጠር እንደሚቻል ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ገርድ ሙለር ተናገሩ።

“ከረሀብ ነፃ ዓለም” ዓለም አቀፍ ጉባዔ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

“ከረሀብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የአቡዳቢ አልጋወራሽ ግርማዊ ሼህ ኻሊድ ቢን መሃመድ ቢን ዛይድ፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት፣ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ገርድ ሙለር እና ጥሪ የተደረገላቸው የጉባኤው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል።

የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ገርድ ሙለር በዚሁ ወቅት በዓለም ላይ ረሃብ ትልቅ ፈተና መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ትልቅ ፈተና በአለም አቀፍ ፖለቲካ እና በመንግስታቱ ድርጅት ዋና አጀንዳ ሆኖ መቀመጥ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ምድር ሁሉንም የመመገብ አቅም እንዳላት አንስተው፤ የረሃብ አደጋን ለማስወገድ የጋራ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ይህንን እውን ለማድረግ በተለያየ እና በአዲስ መንገድ ማካፈልን መማር እንደሚገባ ጠቁመው፤ በሀብታሞች እና በድሆች መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መቀጠል እንደሌለበትም አንስተዋል።

የገበያዎች እና የሉላዊነትን ፍትሃዊነት ለማረጋገጥ ትኩረት መደረግ እንዳለበትም አመላክተዋል።

አፍሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ ቁልፍ ሚና እንዳላትና ለወደፊትም ትልቅ አቅም እንዳላት ዳይሬክተሩ አንስተዋል።

አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እንዲሁም በቀጣዮቹ ጊዜያት ረሃብን ለመዋጋት ተጨማሪ ኢንቨስትመንት ማውጣት እንደሚገባ አመልክተው፤ ሀገራትም ለዚህ ከፍተኛ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው መጠቆማቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ በምግብ ምርታማነት ላይ ላስመዘገበችው ለውጥ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለሰጡት አመራር አድናቆታቸውን ገልፀዋል።

ጉባዔው እስከ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቀጥል ይሆናል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review