AMN- ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ፍስሐ ጥበቡ በሰጡት መግለጫ፤ ቢሮው የንግዱ ዘርፍ ፍትሃዊ፣ ተወዳዳሪና ተደራሽ እንዲሆን የሚያስችል ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት መዘርጋቱን አንስተዋል።
በዚህም በ11ዱ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የኦንላይን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን ቀልጣፋና ፈጣን ማድረግ እንደተቻለም ነው የተናገሩት።
ይሁንና የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ የቴክኖሎጂ አሠራር ሥርዓት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል በሰባት ክፍለ ከተሞች 339 የሚሆኑ ህገ-ወጥ አካውንቶች በመክፈት አገልግሎት ሲሰጡ መገኘታቸውንም አረጋግጠዋል።
በተከፈተው ሐሰተኛ አካውንት ግብር ሳይከፍሉ የንግድ ፈቃድ እድሳት፣ አዳዲስ የንግድ ፈቃድ፣ ዘርፍ መቀየርና የካፒታል ለውጥ አገልግሎት ሲሰጥ መገኘቱን ገልጸዋል።
ሐሰተኛ የኦንላይን አካውንት ከፍተው ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በመመሳጠር የንግድ ሥርዓቱን እንዳይሳለጥ ሲሰሩ የነበሩ በየደረጃው የሚገኙ 136 ሠራተኞችና አመራሮች ላይም ሕጋዊ እርምጃ መወሰዱን ነው የተናገሩት።
በሠራተኞችና በአመራሮች ላይ ከዲሲፕሊን ቅጣት እስከ ሥራ መባረር የሚደርስ እርምጃ መውሰዱንም ጠቁመዋል።
በሐሰተኛ የኦንላይን አካውንት አገልግሎት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የተሰጡ 430 አገልግሎቶች ሥራ ላይ እንዳይውሉ መደረጉንም አያይዘው ገልፀዋል።
የኦንላይን አገልግሎት አሰጣጡን በየጊዜው በማሻሻል ህገ-ወጥ አሠራሮች የመከላከልና በማዕከል የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎችን የማጠናከር ሥራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕብረተሰቡም በተቋሙ ትክክለኛ አካውንት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚያገኝ አስረድተው፤ በተሳሳተ አካውንት የሚሰሩ ሰዎችንም እንዲያጋልጥ ጠይቀዋል።
በፋሲል ጌታቸው