AMN – ጥቅምት 29/2017 ዓ.ም
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር የሲሚንቶ ምርት አቅርቦት እና ፍላጎት ማጣጣም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት አድርገዋል።
ሚኒስትሩ በፍጥነት እያደገ ባለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፉ ድርሻ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይሁንና ለዘርፉ ስራ ቁልፍ የሆነው የሲሚንቶ ዓመታዊ አቅርቦቱ ከ7 ሚሊዮን ቶን አለመዝለሉን አመልክተዋል።
አምራቾች በአቅርቦት በኩል ያለዉን ማነቆ ለመፍታት የማምረት አቅማቸውን ወደ 80 በመቶ በማድረስ 20 ሚሊዮን ቶን ሀገራዊ የሲሚንቶ ምርት ዓመታዊ ፍላጎትን ለማሟላት በትኩረት እንዲሰሩም አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም በሚኒስቴሩ በኩል ይደረግ የነበረው የሲሚንቶ ግብይት ትስስር ሥራ ከዛሬ ጀምሮ መቅረቱንም ነው የጠቆሙት።
አምራቾች በራሳቸው ኃላፊነት በሚመርጧቸዉ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች በኩል ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያቀርቡም ነው ያመላከቱት።
መንግስት የሲሚንቶ ገበያውን ለማረጋጋት ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የአፈጻጸም ሪፖርት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በማያቀርቡ በማናቸውም የሲሚንቶ አምራቾች ላይ የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት ሚኒስትሩ።
አዲሱን የመንግስት ውሳኔና አቅጣጫ ተከትሎ በግብይት ሰንሰለቱ የደላላ ጣልቃ ገብነት የከሰመ ፣ ለመንግስት ፕሮጀክቶችና ለተጠቃሚው ሕብረተሰብ አስተማማኝ የሲሚንቶ አቅርቦት የተረጋገጠ እንዲሆን እና አምራቾችም ተገቢውን ትርፍ እያገኙ የፋብሪካዎቻቸውን ዘላቂ ዕድገት እንዲያረጋግጡም አስገንዝበዋል።
የግብይት ስርዓቱም ሙሉ በሙሉ ከጥሬ ገንዘብ ክፍያ ነጻ ሆኖ በዲጂታል ክፍያ ሥርዓት እንዲፈጸም አቅጣጫ መቀመጡንም ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።