
AMN- ህዳር 3/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ስራ መጀመራቸው ውድድርን መሰረት ያደረገ የፋይናንስ ዘርፍ እድገት እንዲኖር እንደሚያደርግ የግል ምንዛሬ ቢሮ ኃላፊዎች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋፋት እንዲሁም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማዳበር ባወጣው መመሪያ መሰረት አስፈላጊውን መስፈርት ላሟሉ አምስት ባንክ ላልሆኑ የግል ምንዛሪ ቢሮዎቹ ፈቃድ መስጠቱ ይታወሳል።
የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በሙሉ ተቀባይነት ያላቸው የውጭ ሀገር ጥሬ ገንዘቦችን በመግዛትና በመሸጥ እንዲሁም ከባንኮች ጋር በመቀናጀት ለወጪና ገቢ ንግድ የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማመቻቸት የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ ገበያ ለማስፋፋትና ለማዳበር የሚረዳ ሚና እንዳላቸው በመመሪያው ላይ ተመላክቷል።
የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ኃላፊዎች፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ በፋይናንስ ዘርፉ ላይ የተደረገው ለውጥ የውጭ ምንዛሬ ግኝት አማራጭን ለማስፋት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ፎሬክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኤፍሬም ተስፋዬ፤ የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ በውድድር ላይ የተመሰረተ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
ማሻሻያው የግሉን ዘርፍ በማሳተፍ የውጭ ምንዛሬ አገልግሎትና ተደራሽነትን ለማስፋት ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀም ወደ ዘርፉ መግባታቸውንም ነው የገለጹት፡፡
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዴክላራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ፣ የጉምሩክ ፈቃድ በማቅረብ ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ በመመሪያው ተቀምጧል፡
በተመሳሳይ ተፈላጊ የጉዞ መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ፣ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ እንደሚችሉም ነው ብሔራዊ ባንክ የገለጸው።

በዚህ መሰረት በቀን ከ10 እስከ 15 ሺህ የአሜሪካን ዶላር እየገዙና እየሸጡ እንደሚገኙ በማስረዳት በቀጣይም አገልግሎቱን አስፍተው እንደሚሰጡ ጨምረው ገልጸዋል።
ሌላኛው የውጭ ምንዛሬ ፈቃድ አግኝቶ ወደ ስራ የገባው የሮበስት ቢዝነስ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጌጡ ሙሊሳ በበኩላቸው የግል ምንዛሬ ቢሮዎች በዘላቂነት ህጋዊነትን ለማስፈን አጋዥ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በውድድር ላይ የተመሰረተ ምጣኔ ሃብት ለመገንባት ለግል ዘርፉ ይዞ የመጣውን እድል በመጠቀም ዘርፉን መቀላቀላቸውንም አስታውሰዋል።
የግል ምንዛሬ ቢሮዎች መከፈታቸው አማራጭ የውጭ ምንዛሬን ግብይትን በማስፋት የውጭ ምንዛሬ ክምችትን ለማሳደግ ፋይዳቸው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።
ባንክ ያልሆኑ ምንዛሪ ቢሮዎች የጥቁር ገበያ ልዩነትን በማጥበብና አማራጮችን በማስፋት በሂደት ጥቁር ገበያውን ለማክሰም እንደሚያግዝም ነወ የገለጹት፡፡
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት 80 በመቶ መጨመሩን የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ የማሻሻያውን የሶስት ወራት አፈጻጸም ሪፖርት አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ መግለጻቸው እንደሚታወስ ኢዜአ ዘግቧል፡፡