ኬንያ የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት ተሞክሮ እየወሰደች ነው

AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም

ኬንያ ዋና ከተማዋ ናይሮቢን ፅዱ የማድረግ ዘመቻን አጠናክራ ቀጥላለች።

የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ በተካሄደው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባኤ ላይ መታደማቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንቱ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ኢትዮጵያ ረሃብን ለመዋጋት እየሠራች ያለችውን እንዲሁም ለዜጎቿ ምቹ አካባቢ ለመፍጠር እየሄደች ያለችበትን ሁኔታም አድንቀው ነበር።

ከጉባኤው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ሀገራቸው እንደተመለሱም ከናይሮቢ ከተማ አስተዳደር፤ ከፓርላማ አባላት፤ ከመዲናዋ ምክር ቤት አባላት እና ከከተማዋ የወንዞች ኮሚሽን ኃላፊዎች ጋር በከተማዋ ልማት ላይ ተወያይተዋል።

ናይሮቢ የሀገሪቷ ዋና ከተማ እና በምሥራቅ አፍሪካ የብዙ ሀገራት መግቢያ በር በመሆኗ በሀገሪቷ የልማት ዕቅድ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ እንደሚሰጣት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ጠቁመዋል።

ማታሬ፣ ናይሮቢ እና ንጎንግ የተባሉ በከተማዋ የሚገኙ ወንዞችን ለማፅዳት እና ለማልማት በተያዘው መጠነ-ሰፊ ዕቅድ ዙሪያ ለፓርላማ አባላቱ እና ለባለሥልጣናቱ ሰፊ ማብራሪያ መደረጉንም ነው የገለጹት።

ከዚህም ባሻገር በመዲናዋ ዘመናዊ መንገዶችን መዘርጋት፣ በከተማ ውስጥ የመንገድ መብራቶችችን ማዘመን እንዲሁም ትምህርት ቤቶችን ማስፋፋት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ጥልቅ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል።

የከተማዋን ወንዞች መልሶ የማልማት ኢንሼቲቭ ቀደም ብሎ የተጀመረ ቢሆንም የዘመናዊ መንገዶች ዝርጋታው እና የመንገድ መብራቶችችን የማዘመኑ ሥራ በቅርብ ጊዜ የተጀመረ መሆኑ ልብ ይሏል።

የከተማዋን ወንዞች መልሶ የማልማት ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ ወደ 20 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች በየወሩ በሚካሄደው ዘመቻ ላይ በመሳተፍ 94 ኪ.ሜ ከሚሸፍኑ የናይሮቢ፣ ንጎንግ እና ማታሬ ወንዞች ላይ እስካሁን ከ75 ኪ.ሜ ላይ ቆሻሻን የማፅዳት ሥራን መሥራታቸውን በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።

የወንዝ ዳርቻዎቹን ለማልማትም እስካሁን 272 ሺህ ችግኞች መተከላቸውን እና 268 የችግኝ ማፍያዎች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review