የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት የዕድሳት ሰራ ታሪካዊ ቅርጽና ይዘቱን በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ ነው- የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሀንዲሶች

AMN- ህዳር 5/2017 ዓ.ም

የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት የዕድሳት ሰራ በተሻለ የዕውቀት ሽግግር ታሪካዊ ቅርጽና ይዘቱን በጠበቀ አግባብ እየተከናወነ እንደሚገኝ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ መሀንዲሶች ገልጸዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አመራር ሰጭነት በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ከሚገኙ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎች በተጨማሪ የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት ዕድሳትም እየተከናወነ ይገኛል።

የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው፤ የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት የዕድሳት ስራ በቅድመ አያቶች ታንፆ ዘመናትን የተሻገረውን ቅርስ ከመፍረስ እንደሚታደግ ገልጸዋል።

በዕድሳት ሥራው እየተሳተፉ የሚገኙ ዜጎችም ቅርሱን በመታደግ ለቀጣዩ ትውልድ የማሻገር ኃላፊነትን በመውሰድ የራሳቸውን አሻራ እያኖሩ የሚገኙ ታሪክ ሰሪዎች ናቸው ብለዋል።

ደብዝዞ የነበረውን የቀደምት ነገስታት የስልጣኔ ታሪክ በማደስ ለልጅ ልጆቻቸው በኩራት የሚናገሩትን ወርቃማ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑንም ተናግረዋል።

የቢአኤካ ጠቅላላ ንግድ ስራ ድርጅት በጎንደር ከተማ የሚያስገነባቸው ሶስት ፕሮጀክቶች አስታባባሪ ላቃቸው እንየው፤ የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት የዕድሳት ስራ የቅርሱን ታሪካዊ ቅርጽና ይዘት በመጠበቅ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የቅርሱ ዕድሳትም ከ800 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ ዕድል ፈጥሯል ያሉት አስተባባሪው፤ መንግስትና ማህበረሰቡም ለዕድሳት ስራው ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በቢአኤካ ጠቅላላ ንግድ ስራ ድርጅት የፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር መሳፍንት ካሳው፤ የአፄ ፋሲለደስ አብያተ መንግስት ዕድሳትን ቀን ከሌሊት እያፋጠኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዕድሳት ሥራው በታሪካዊ የኪነ ህንፃ ዕድሳት የዕውቀት ሽግግር እየተፈጠረበት እንደሚገኝ መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review