የቻይና -አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

AMN-ኅዳር 5/2017 ዓ.ም

የቻይና-አፍሪካ የኢኮኖሚ እና የንግድ ትብብር ጉባኤ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።

ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ የገባው የቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ከፍተኛ የልዑካን ቡድንም በጉባኤው እየተሳተፈ ይገኛል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ እና ቻይና የቆየና ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አላቸው።

ቻይና በንግድ፣ በኢንቨስትመንትና መሰረተ ልማት ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዳላት ገልጸው እየተካሄደ ያለው የኢኮኖሚና ንግድ ትብብር ጉባኤ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።

የቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ባለሀብቶች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች እንዲሰማሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቺን ሃዪ(Chen Hai) በበኩላቸው ጉባኤው ቻይና ከኢትዮጵያና ከአፍሪካ ጋር ያላትን የንግድና ምጣኔ ሃብት ትብብር የበለጠ እንደሚያጠናክረው ጠቁመዋል።

የቻይናዋ ጂያንሱ ግዛት ዋና ገዥ ሹ ኩሊን የግዛቷን የምጣኔ ሃብትና ኢንቨስትመንት አቅም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ የጂያንሱ ግዛት ንግድና ኢንቨስትመንት ጠንካራ አጋር ስትሆን በአሁኑ ወቅትም የግዛቷ በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ ኢንቨስትመንት ዘርፎች በኢትዮጵያ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይም ከአፍሪካ ጋር በግብርና፣ በመሰረተ ልማት፣ በኢንዱስትሪና ሌሎች የትብብር መስኮች ጠንካራ አጋርነት ለመፍጠር እንሰራለን ነው ያሉት።

ጉባኤው በቻይና እና አፍሪካ መካከል ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር የገለጹት ደግሞ የአፍሪካ ህብረት የግብርና፣ ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ አካባቢ ከፍተኛ አማካሪ ሊአላ ሎኮሳንግ(ዶ/ር) ናቸው።

በአህጉሪቱ የመሰረተ ልማት፣ ግብርና፣ ንግድ፣ የግብርና ማቀነባበሪያ ዘርፎችን ጨምሮ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።

በጉባኤው የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች፣ የአፍሪካ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የኢትዮጵያ የቢዝነስ ማህበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

በኢትዮጵያ ስለሚገኙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ገለጻ ተደርጓል።

ጂያንሱ የቻይናዋ ሁለተኛዋ ግዙፍ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ግዛት ስትሆን 76 ኩባንያዎቿ በኢትዮጵያ ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሚያወጡ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review