ሥራ ፈጣሪዎች ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ሚና አላቸው – ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

AMN- ህዳር 9/2017 ዓ.ም

ሥራ ፈጣሪዎች እምቅ አቅምን ወደ ተግባር በመቀየር ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ሚና አላቸው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከአንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር ያዘጋጁትና በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የአንተርፕረነር ሳምንት ማስጀመሪያ መርሃ ግብር እየተካሄደ ነው።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በመርሐ ግብሩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር፥ ሥራ ፈጣሪዎች ሀብቶችን አሟጦ ለመጠቀምና ዕውቀት መር ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብለዋል።

አንተርፕረነርሺፕን በመላ ሀገሪቱ ለማስፋፋትና ውጤታማ ስራ ፈጣሪዎችን ለማብዛት ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሰፊ ስራ መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው በተያዘው ዓመት ይህን ማስፋት የሚያስችሉ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት።

የአንተርፕርነር ሳምንት በተለያዩ ሁነቶች የሚከበር ሲሆን ይህም የውስጥ አቅምን ማነቃቃትና ከዓለም ጋር ማስተሳሰር እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ኢንተርፕረነርሺፕ ዘላቂና አስተማማኝ ኢኮኖሚ ለመገንባት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።

በቴክኖሎጂ የተደገፈ ስራ ፈጠራን ለማበረታታትና ስራ ፈጣሪዎች ሀሳባቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ምቹ የፖሊሲ ማዕቀፎችና ህግጋት መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።

በዓለም ለ16ኛ በኢትዮጵያ ለ10ኛ ጊዜ መከበር በጀመረው የአንተርፕረነርሺፕ ሳምንት የተለያዩ ሥራ ፈጣሪዎች የስራ ውጤቶችን የሚያሳይ ኤግዚቪሽንና ባዛርም መከፈቱን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review