
AMN- ህዳር 9/2017 ዓ.ም
በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ወታደራዊ ግንኙነት ለቀጣናዊ መረጋጋት፣ ለፀረ ሽብርተኝነት ትግልና ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ሆኖ መቆየቱን የመከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ገለጹ።
ኢንጂነር አይሻ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች የመከላከያ ረዳት ፀሃፊ ማውሪን ፋሬል የተመራውን የልዑካን ቡድን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡
በውይይታቸውም ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር ላላት የረዥም ጊዜ ወታደራዊ ግንኙነት ትልቅ ዋጋ እንደምትሰጥና ይህንኑ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር እንደምትፈልግ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለው የሁለትዮሽ ወታደራዊ ግንኙነት ለቀጣናዊ መረጋጋት፣ ለፀረ ሽብርተኝነት ትግልና ለሰላም ግንባታ ወሳኝ ሆኖ መቆየቱንም አንስተው፤ በአሜሪካ መከላከያ እገዛ በኢትዮጵያ የሚተገበሩ በርካታ ፕሮግራሞች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
ረዳት ፀሀፊዋ በበኩላቸው፤ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር በተለይ በፀጥታና ሰላም ያላትን የቆየ ወታደራዊ ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡