የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ፣ ህጋዊ ደረሰኝ የመቁረጥ እና የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተከናወነ ነው፡- አቶ ጃንጥራር አባይ

  • Post category:ልማት

AMN – ኅዳር 10/2017 ዓ.ም

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ተደራሽ የማድረግ ፣ ህጋዊ ደረሰኝ የመቁረጥ እና የከተማዋን ነዋሪ ተጠቃሚ የማድረግ ስራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡

ከምክር ቤት አባላት በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ምላሽ የሰጡት አቶ ጃንጥራር አባይ የነገዋ የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማእከል ስልጠና በመስጠትና የስራ እድል ከመፍጠር አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እንዲሁም ውጤት የተገኘበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህን መሰል ማእከል በሁሉም ክፍለ ከተሞች ማዳረስ ከበጀት አኳያ እንደማይቻል ነገር ግን በሂደት እየሰፋ መሄድ እንዳለበት አንስተዋል፡፡አሁን ላይ ይህንን ማእክል ማጠናከር ፣ማበልጸግ እና ማደራጀት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የወጣቶች የስብእና መገንቢያ ማእከላት ወደ ስራ አለመግባትን በተመለከተ ጉዳዩን ፈትሾ ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባ እና ማስተካከያ እንደሚደረግ ያነሱት አቶ ጃንጥራር እስከ አሁንም ማእከላቱ ወደ ስራ ሳይገቡ መዘግየት እንዳልነበረባቸው ተናግረዋል፡፡

የአርሶ አደሮችን የይዞታ ካርታ በተመለከተ መመሪያውን ተግባዊ በማድረግ ረገድ መዘግየት አለ ያሉት አቶ ጃንጥራር ይህ ስራ እስካሁንም ማለቅ እንደነበረበት አስታውቀዋል፡፡ ይህም ከመረጃ አለመጥራት ጋር ተያይዞ መዘግየቱን አንስተዋል፡፡

ችግሩን አርሞ በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ስራውን ለመጨረስ አቅጣጫ መያዙን አንስተዋል፡፡

ከመስሪያ ቦታዎች ጋር ተያይዞ ከምክር ቤት አባላት ለተነሳው ጥያቄም 110 የመስሪያ ቦታዎችን በመመሪያው መሰረት በማስለቀቅ ለተጠቃሚዎች ማስተላለፍ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ረገድ ተጠቃሚ የሚሆኑ ዜጎችን በመለየት ተጠቃሚ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ረገድ ሰፊ ችግር እንደሌለም ጠቁመዋል ፡፡

የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎትን ከማቅረብ አኳያ ላለፉት ዓመታት ትልቅ ስራ መሰራቱን ያወሱት አቶ ጃንጥራር ፡፡ በትራንስፖርት ተደራሽ ያልሆኑ አካባቢዎችን በመለየት የትራንስፖርት አገልግሎቱ እንዲሰፋ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ተበተለይም ላለፉት 2 እና 3 ዓመታት አውቶቡሶችን በመግዛት በማሰማራቱ በኩል ጥሩ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡

በመልሶ ማልማት ተነሺ የሆኑ እና አቃቂ ፣ገላን፣ ጉራ እና አራብሳ አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል ምክትል ከንቲባው፡፡

በእነዚህ አካባቢዎች የአውቶቡሶችን ስምሪት ጨምሮ የተለያዩ መሰረተ ልማቶች እንዲሟሉ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

ከሰነድ አልባ ይዞታዎች ጋር ተያይዞ መመሪያ መኖሩን ያወሱት አቶ ጃንጥራር ማንኛውም ሰነድ አልባ ሰነድ አልባ የሚያሰኘው ሁኔታ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ይህ ስራ ፈጥኖ ማለቅ የነበረበት ስራ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡

ትክክለኛ ሰነድ አልባ ሆነው ሰነድ ያልተሰጣቸውን ችግር በመፈተሽ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ከደረሰኝ መቁረጥ ችግር ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጥያቄ በተመለከተ በከተማዋ ሁሉም አካባቢዎች ደረሰኝ የመቁረጥ ስራ መከናወን እንዳለበት ተወስኖ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ረገድም ግብረሀይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል፡፡ይሁንና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በተደረገ ውይይት ደረሰኝ አንቆጥርም የሚል ሀሳብ እንደሌለ ነገር ግን ትኩረቱ ጅምላ እና አከፋፋዮች ላይ መሆን እንዳለበት ከስምምነት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ረገድ ውይይቱ መቀጠሉን እና በጉዳዩ ላይ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

በከተማዋ የሚሰራው የልማት ስራ ገቢን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ደረሰኝ እየቆረጡ የገቢን መሰረት ማስፋት፣ህጋዊነትን ማስፈን ፣በህግ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችን መብት መጠበቅ እንደሚገባ እና በዚህ ረገድ የምክር ቤት አባላትም እገዛ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

ትልቁ የገቢ ማእከል የሆነው መርካቶን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በተለይም ከገቢ ደረሰኝ መቁረጥ እና ከባለሙያ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ችግሮች እየታረሙ የሚሄዱ መሆናቸውንም አቶ ጃንጥራር አስረድተዋል፡፡

በሰለሞን በቀለ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review