
AMN- ኅዳር 11/2017 ዓ.ም
ብልጽግና ፓርቲ የአቅመ ደካማ ወገኖችን ቤት በማደስና በመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለፁ።
የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት በአሶሳ ከተማ ለአቅመ ደካሞች ያስገነባቸውን መኖሪያ ቤቶች አስረክቧል።
ቤቶቹ ሙሉ የቤት መገልገያ ቁሳቁስ የተሟላላቸው እንደሆኑም ተገልጿል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ ብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር ስራዎችን በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል።
በዚህም የአቅመ ደካማ ቤቶችን በመገንባት ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል።
ሰው ተኮር ስራዎችና ቃልን በተግባር መፈፀም የብልጽግና ፓርቲ መለያ ነው ያሉት አቶ አደም ፋራህ በየደረጃው ያሉ የፓርቲው መዋቅሮች አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በተጠናከረ መልኩ መወጣት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።
ፓርቲው የዜጎችን ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
ቤታቸው የታደሰላቸውና እንደ አዲስ የተገነባላቸው ነዋሪዎች ለተደረገላቸው የቤት እድሳትና ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በቁልፍ ርክክቡ ወቅት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ጨምሮ የዋናው ጽህፈት ቤት፣ የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።