AMN- ህዳር 12/2017 ዓ.ም
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ ( ዶ/ር ) ራሱን “ፋኖ” ብሎ የሚጠራው ጽንፈኛ ቡድንና ሸኔ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን አስገነዘቡ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው የራሴ የሚሉትንም የጣላቴ የሚሉትን በአምላክ አምሳያ የተፈጠረውን ክቡር የሰው ልጅ ህይወትን አውሬ እንኳን በማይፈጽመው መልኩ በአስከፊ ሁኔታ በሁሉም አማራጮች ይገድላሉ ብለዋል።
ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ሰላሌ -ደራ አካባቢ ጽንፈኛው ቡድን የፈፀመው የአረመኔነት ተግበር ይህንኑ የሚያመለክት ነውም ብለዋል።
ይህ ፈጽሞ ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አፀያፊ ድርጊት መወገዝ አለበት።ዓላማቸው ሁለት ነውም ብለዋል።
አንዱ ዓላማ በዚህ አሰቃቂ ድርጊት አንዱ ብሔር በሌላኛው ላይ ተነሳስቶ እልቂትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ማድረግ ነው። በዚህም እኩይ ፍላጎታቸውን ማሳከት ነው።
ሌላኛው ዓላማቸው ደግሞ በዚህ ኢሞራላዊ ድርጊታቸው በህዝብ ዘንድ ፍርሃት በማንገስ ያሻቸውን ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል። ሁለቱም ሞታቸውን ያፋጥነዋል እንጂ የሚሳካ አይደለምም ብለዋል።
ቅዥት እና እኔ ብቻ የሚል ጫፍ የረገጠ ጽንፈኝነት የሚወልደው በመሆኑ እንዲህ አይነት እኩይ ፍላጎት መቼም ቢሆን ተቀባይነት የለውም ብቻ ሳይሆን አይሳካም።
የአንድን ማህበረሰብ ልብ መግዛት የሚቻለው፣ በዚህም የትኛውንም አይነት ፍላጎት ከግብ ማድረስ የሚቻለው ምክንያታዊ በመሆን እና የማህበረሰቡን ህግጋትና ሞራላዊ እሴቶች በመጠበቅ መሆኑንም ሚኒስትሩ አመልክተዋል።
ለማመን የሚከብደን ኢሞራላዊ ድርጊት በመፈፀም በዓለማችን የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ የቆመለትን ግብ ያሳካ የለም። ለጊዜው አንዳንዶቹ ኢሞራላዊ ድርጊቶች አንድን ውጥን ያሳኩ ይመስሉ ይሆናል።
ይህ እንዳልሆነ የፋሽስቶች ታሪክ ምስክር ነው።
በሁለቱም አቅጣጫ ሰሞኑን በሰላሌ ደራ ላይ የተፈፀመው አጅግ ሊወገዝ የሚገባው አይነት ሰውኛ ያልሆኑ ድርጊቶች በመፈጸም አማራና ኦሮሞን ለመጨረስ ያልተሞከረበት ጊዜ የለምም ብለዋል።
ግን ሁሉም አልተሳኩም ብቻ ሳይሆን በዚህ አይነት ኢሞራላዊ ሁኔታ መቼም ቢሆን አይሳካም።
ምክንያቱም የሰው ልጅ በተፈጥሮው ሚዛናዊ፣ ትርፍና ኪሳራን ለይቶ በምክንያታዊነት አቋም የሚወስድና ወደ ድርጊት የሚገባ ነው።
ሸኔ እና ጽንፈኛው ጃውሳ በሚፈጽሙት አሠቃቂ ድርጊቶች ሁለቱን የተወለዱ፣ የተገመዱ፣ ከሌሎች ወንድም እህቶቻቸው ጋር በመሆን በከፈሉት መስዋዕትነት ኢትዮጵያን ያፀኑትን ህዝቦች በማጋጨት የትኛውንም አይነት እኩይ ፍላጎት ማሳካት አይቻልም።
የጽንፈኞች ፍላጎት ከማፍረስ እና ብጥብጥ ከመፍጠር የተሻገረ አይደለም። ፍላጎታቸው የህዝብ ጥቅም እና መብት ማስከበር ቢሆን ለምን ንጹሃንን ፣ ምስኪን፣ ራሳቸውን መካለከል የማይችሉ ሰዎችን ለምን ይገድላሉ ፣ ያርዳሉ፣ ይዘርፋሉ፣ ሴቶች ይደፍራሉ፣ የህዝብና ግለሰቦች ሃብትና ንብረት ያወድማሉ? ዓላማቸው የራሳቸውን እና የሌሎች ሃይሎችን ፍላጎትና ጥቅም ማገልገል ነው።
በእንዲህ አይነት እኩይ ድርጊት የተሰማሩትን አረመኔዎች መላው ህዝብ እና መንግስት በተባበረ ክንድ ሁሉንም አማራጮች ተጠቅመው ስርዓት እንዲይዙ ያደርጋሉ። የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሁሉም ይስተካከላል። እየነፈሰ ያለው ሰላምም ይፀናል ብለዋል ሚኒስትሩ በመልእክታቸው።