የመዝናኛ አምባዎች

  • Post category:ልማት

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች የመዝናኛ ቦታዎች እጥረት ይገጥማቸው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ በተለይ አረንጓዴ ስፍራና ተፈጥሯዊ መልክ ያለው የመዝናኛ ቦታ እጥረት የነበረበትን ልክ በከተማዋ ተወልዶ ያደገ ሰው በቀላሉ የሚገነዘበው ነው፡፡ ነዋሪዎች በተለይም ወጣቶች የልብ መሻታቸውን የሚሞሉ የመዝናኛ ቦታዎችን በቅርበት ባለማግኘታቸው ምክንያት ከከተማዋ ርቀው እስከ መጓዝም ይደርሱ ነበር። አቅም ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ከከተማ በመውጣት ረጅም ርቀትን ተጉዘው እንደ ቢሾፍቱ፣ ሶደሬ እና ላንጋኖ ድረስ በመሄድ ተዝናንተው ይመለሱ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ለመዝናናት ከከተማ ሲወጣም ከርቀቱ አኳያ ውሎ ማደርን መጠየቁ አይቀርም፡፡ በዚህም ለመኝታ፣ ለትራንስፖርትና ለምግብ ብዙ ወጪን ያስወጣል፡፡ የገንዘብ አቅም የሌላቸው ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ወስደው በእነዚህ አካባቢዎች ለማዝናናት ባለመቻላቸው በቤታቸው ሆነው ጊዜያቸውን ያሳልፉ ነበር። ይህ የእያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ አሁን የኮሪደር ልማቱ በከተማዋ የቆዩ መሠል ችግሮችን መፍታት ችሏል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

አዲስ አበባ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሆን አሻራዎችን እያስቀመጠች ትገኛለች፡፡ ወላጆች እንደበፊቱ ልጆቻቸውን የት ወስጄ ላዝናና? ብለው ሳይጨነቁ በየመንገዱ ዳር ቁጭ ብለው የሚዝናኑባቸው፣ የሚጫወቱባቸው፣ የሚቦርቁባቸው የመዝናኛ ቦታዎች ተዘጋጅተዋል። የመንገድ ዳር ማረፊያ ቦታዎች፣ ደማቅ ህብረ ቀለም የሚፈጥሩ ፋውንቴኖች ወይም ፏፏቴዎች ተሰርተዋል፤ ቁጭ ብለው ሻይ ቡና የሚሉባቸው የመዝናኛ ስፍራዎችም በየሰፈሩ ተፈጥረዋል፡፡ ነዋሪዎች ከመኖሪያ አካባቢያዎች ብዙም ርቀው ሳይሄዱ የመዝናኛ ቦታዎችን በቅርብ ማግኘት ችለዋል፡፡

ታድያ የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን ልጆች እና ወጣቶች የመዝናኛ ቦታዎች እጥረትን በእጅጉ እየቀረፈ ስለመሆኑ ነዋሪዎችም ይናገራሉ፡፡ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል የመዝናኛ አማራጭ ሆነው በቀረቡት የሲ.ኤም.ሲ፣ ፒያሳ እና የአራት ኪሎ አካባቢዎች በመገኘት ቅኝት አድርጓል። በስፍራዎቹ አግኝተን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በአዲስ አበባ የተከናወነው  የኮሪደር ልማት ሰፊ የመዝናኛ አማራጮችን እንዲያገኙ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበረከቱን ገልፀዋል፡፡

በሲ.ኤም.ሲ በተለምዶ የተባበሩት ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ከጓደኞቹ ጋር የእግር ጉዞ እያደረገ አግኝተን ያነጋገርነው ወጣት አብርሃም ጥላሁን፣ በፊት እነዚህ አካባቢዎች የቆሻሻ መጣያ እና አላፊ አግዳሚው ሁሉ የሚፀዳዳባቸው እንደነበር ተናግሯል፡፡ አክሎም፣ አሁን በኮሪደር ልማት አማካኝነት ተሰርቶ ለነዋሪዎቹ መዝናኛ እንዲሁም ለአካባቢው ደግሞ ተጨማሪ ውበት እና ገጽታን አላብሷል ብሏል፡፡

በስፍራው በነበረን ቆይታ በአካባቢው የሚያልፉ ሁሉ የተሰራውን ቦታ በመደነቅ ሲመለከቱ ለመታዘብ ችለናል፡፡ በአካባቢውም በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የእግር ጉዞ ያደርጋሉ። በመንገዱ ዳርቻዎች ፈጣን ምግቦችና የተለያዩ የመጠጥ አይነቶች ይሸጣሉ፡፡ አላፊ አግዳሚዎች እና በመንገድ ጠርዝ በተሰሩ መቀመጫዎች አረፍ ብለው ዙሪያ ገባውን የሚማትሩ ሰዎች ፊት ላይ የደስተኝነትና የተስፋ ስሜት ይታያል፡፡

ህጻናት በተለያዩ ህብረ ቀለማት አሸብርቆ በሚወረወረው ውሃ ውስጥ እየገቡ በደስታ ይፈነጥዛሉ፤ ይቦርቃሉ፤ ጓደኛሞች ቁጭ ብለው የልብ የልባቸውን ይጫወታሉ፡፡ አካባቢውን ተዟዙሮ ለተመለከተው ሁሉ ሃሴትን ያላብሳል፡፡

ወጣት አብርሃም ጥላሁን የተሰራው ስራ የከተማዋ ነዋሪዎች የመዝናኛ ቦታዎችን እጥረት የመለሰ ነው ብሏል፡፡ በፊት የከተማዋ ልጆች የሚዝናኑባቸው ቦታዎች በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ምክንያት ወጣቶች በአልባሌ ቦታዎች በመዋል ለሱስና ለሌሎች ጉዳዮች ሲዳረጉ እንደነበር ይናገራል፡፡ በመዝናኛ ቦታ እጥረት ምክንያት ህጻናት ቤታቸው ውስጥ ተደብቀው ይውሉ ነበርም ይላል፡፡

አካባቢው የቆሻሻ መጣያ ነበር የሚለው ወጣቱ ዙሪያውን በሚያምር ዲዛይን ፋውንቴን በመስራት ነዋሪዎች ቁጭ ብለው እንዲዝናኑበት፣ የእግር ጉዞ እንዲያደርጉበት መመቻቸቱን ተናግሯል፡፡ በአካባቢው የመዝናኛ ቦታው መጸዳጃ ቤት የተሟላለት መሆኑን ገልጿል፡፡ ነዋሪዎች በየሰፈራቸው የመዝናኛ እና የመናፈሻ ቦታዎች መሰራታቸው ለነዋሪዎቹ እፎይታን ለከተማዋ ደግሞ ውበትን ማጎናጸፉንም ያስረዳል፡፡

አሁን ወጣቱ ቁጭ ብሎ ከጓደኞቹ ጋር የሚጫወትበትን ጤናማ ስፍራ አግኝቷል፡፡ በርካታ ወጣቶች ከመኪና ጭስ ወጥተው በዚህ ስፍራ ንጹህ አየር በመሳብ እየተዝናኑ ነው፡፡ በኮሪደር ልማት እንደዚህ ዓይነት የመዝናኛ ቦታ መሰራቱ የመናፈሻ ቦታ ማግኘት ችግር ሆኖባቸው ለነበሩ ለከተማዋ ነዋሪዎች እፎይታ ሰጥቷልም ባይ ነው፡፡

ወጣት ቢታኒያ እዮብ በመናፈሻ ቦታው ከሴት ጓደኛዋ ጋር የእግር ጉዞ በማድረግ ላይ ሳለች አግኝተን ነው ያነጋገርናት፡፡ “በልጅነት እድሜያችን መናፈሻ ቦታ ማግኘት ብርቅ ሆኖብን ነበር፤ ወጥተን የምንዝናናበት ቦታ ባለመኖሩ ቤታችን ውስጥ ሆነን አብዛኛውን ጊዜ እናሳልፍ ነበር፡፡ አሁን ግን ነገሮች እየተቀየሩ ነው” ብላለች፡፡

በመዝናኛ ቦታዎች እጥረት ምክንያት ወጣት ቢታኒያ እና ጓደኛዋ ወጥተው ተዝናንተው እንደማያውቁም ትገልጻለች፡፡ አሁን ግን በኮሪደር ልማቱ የመዝናኛ ስፍራዎች በየቦታው በመሰራታቸው ወጥተን መንፈሳችንን እያደስን ወደ የቤታችን እንድንመለስ አስችሎናል ብላለች።

የአራት ኪሎ እና የፒያሳ አካባቢ ነዋሪዎች በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ውብ ገፅታን በተላበሱት የአካባቢው ጎዳናዎች ወጥተው ሲዝናኑ በቅኝታችን ወቅት አይተናል። በአካባቢዎቹ የተሰሩ የመዝናኛ ቦታዎች በሰዎች ተጥለቅልቀው መዋል ከጀመሩም ሰነባብቷል፡፡ በአራት ኪሎ አካባቢ በተሰራው የሳይክል መንገድ ወጣቶች ሳይክል በመንዳት ይዝናናሉ፣ በእግረኛ መንገድ ነዋሪዎቹ ይንሸራሸራሉ፤ እንደልባቸው የፈለጉበት ቦታ ደርሰው ይመለሳሉ፡፡

አቤኔዘር አረጋ በሲኤምሲ የተባበሩት አካባቢ የተሰራውን የመዝናኛ ቦታ በግርምት እየተመለከተ ያገኘነው ሌላው ወጣት ነው። የከተማዋ ነዋሪዎች የነበረባቸውን የመዝናኛ ቦታዎች እጥረት እና አሁን የተሰራላቸውን የመዝናኛ ቦታ ከበፊቱ ጋር እያነጻጸረ ሀሳቡን አጋርቶናል፡፡ የኮሪደር ልማቱ ዘርፈ ብዙ የከተማዋን ውስብስብ ችግር የፈታ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የመዝናኛ ቦታ በማጣት ምክንያት የልጅነት እድሜውን ከጓደኞቹ ጋር እንደፍላጎቱ ሳይዝናና ሳይቦርቅ ማሳለፉን በቁጭት የሚያስታውሰው ወጣት አቤኔዘር፣ የከተማዋ ልጆች ወጥተው ለመዝናናት ይቅርና ንጹህ አየር እንኳን ይናፍቃቸው ነበር ብሏል፡፡ እግረኛው ከመኪና ጋር ተቀላቅሎ ይሄድ ነበር፤ በዚህም እግረኞች የመኪና አደጋ ይደርስባቸው ነበር ይላል፡፡ የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ የተሰራው የመዝናኛ ቦታ በፊት የነበረውን ችግር እየቀረፈ ነው ሲልም አክሏል፡፡

በአራት ኪሎ አካባቢ በተሰራው የእግረኛ መንገድ ዳር ወጣቶች ቁጭ ብለው ይጫወታሉ፡፡  በመንገድ ዳር በተሰሩ የፈጣን ምግብ አገልግሎት መሸጫ ቦታዎች ቁጭ ብለው እየተጫወቱ የደረሰውን ምግብ እየተመገቡ ሻይ ቡና ይላሉ። በአካባቢው ለተዘዋወረ ሰው ሁሉ ቦታው ልዩ የደስታ ስሜትን ይፈጥራል፡፡ የኮሪደር ልማቱ የነዋሪዎችን የመዝናኛ ቸግርን በእጅጉ ቀርፏል ያስብላል፡፡ እኛም ተዟዙረን ምልከታ በአደረግንባቸው ቦታዎች ሁሉ የተረዳነው ይህንኑ ነው፡፡

አቶ ከድር ጃቢር በአራት ኪሎ አካባቢ መንገድ ዳር በተሰራው የመዝናኛ ቦታ ላይ ቁጭ ብለው ያገኘናቸው አባት ናቸው፡፡ በተለምዶ አስኮ በሚባል የከተማዋ አካበቢ የሚኖሩት አባት በፊት ልጆቻቸውን ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ ወይም ሳሪስ ወደሚገኘው የብሔረጽጌ መናፈሻ በመውሰድ በማዝናናት ይመልሱ ነበር፡፡ ሆኖም ብሔረጽጌ ድረስ ልጆቻቸውን አዝናንተው ለመመለስ ይርቃቸው እንደነበር፤ ቀላል ለማይባል የትራንስፖርት ወጪ ይዳረጉ እንደነበርም ይገልጻሉ፡፡ አሁን የኮሪደር ልማቱን ተከትሎ በየአካባቢው የተሰሩ የመዝናኛ ቦታዎች የልጆችን የመዝናናት ፍላጎት የመለሱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ መዲናዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ተስማሚ የመዝናኛ ከተማ እያደረጋት ይገኛል ያሉት አቶ ከድር፣ ነዋሪዎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱበት፣ የሚኖሩበት፣ የሚዝናኑባቸው ቦታዎች ተፈጥረዋል፡፡ ከተማዋ አሁን በመዝናኛ እና በአረንጓዴ ቦታዎች ልማት ረገድ መልካም በሚባል ደረጃ ላይ ትገኛለች የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ኅብረት ዋና መቀመጫ፤ የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና መቀመጫ ከተማ ስትሆን በዓለም ካሉት የዲፕሎማቲክ ከተሞች አንዷ ናት፤ መዲናዋ ያላትን ፀጋ ሳትጠቀም መቆየቷን ችግሩን ግምት ውስጥ በማስገባት አዲስ አበባ ዳግም እየለማችና የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን የሚያጠናክር ደረጃ እንድትይዝ የኮሪደር ልማቱ ወሳኝ ልማት ስለመሆኑም የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይናገራሉ። ይህንን ሀሳብ ከሚያጠናክሩት ባለሙያዎች መካከል የምጣኔያዊ ሀብት ተንታኝ የሆኑት አቶ ኪሩቤል ሰለሞን ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከተማዋ ቀደም ሲል የመብራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ፣ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን ጨምሮ ሰፋፊ ችግሮች እንደነበሩባት የተናገሩት አቶ ኪሩቤል፣ የኮሪደር ልማቱ የሕዝብ መዝናኛዎችንና ማረፊያዎችን ማስፋፋት ላይ ትኩረት በማድረግ በመሰራት ላይ ይገኛል፡፡ የከተማዋን ነዋሪዎች የመዝናኛ ስፍራ ችግር ከማቃለል አልፎም የቱሪዝም መዳረሻነቷን በማላቅም ከተማዋ ተጨማሪ ገቢ የምታገኝበትን ዕድል ይፈጥራል ብለዋል፡፡

የመጀመሪው ዙር የኮሪደር ልማት ስራ 32 የውሃ ፏፏቴዎች፣ 20 ሄክታር የሚሸፍን መልሶ ማልማት፣ 8 ወንዞችን በተቀናጀ መልኩ ማልማት፣ 120 ዘመናዊ የመንገድ ዳር የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ ከ50 ሄክታር በላይ የከተማ አረንጓዴ ልማት ሥራዎች እንዲሁም 70 የሕዝብ መናፈሻ ሥፍራዎች እና የፈጣን ምግብ አገልግሎት መሸጫ ቦታዎች ያካተተ ነው፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review