AMN ህዳር 16/2017 ዓ .ም
ኢትዮጵያ እና ቻይና በሳይበር ደህንነት መስክ ያላቸውን ትብብር ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሀሚድ፤ በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።
ውይይቱ በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት በሳይበር ደህንነት ላይ በጋራ በሚሰሩባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።
የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሃሚድ፤ ተቋሙ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ያለማቸውን ምርት እና አገልግሎቶችን እንዲሁም በተለያዩ የሳይበር ደህንነት ዘርፎች እየተሰሩ የሚገኙ ስራዎችን አስመልክቶ ለአምባሳደሩ ገለጻ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ከቻይና መንግስት ጋር በተለያዩ የልማት ዘርፎች እያከናወናቸው የሚገኘውን ጠንካራ የትብብር ስራዎችን በሳይበር ደህንነት ዘርፍም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ቼን ሃይን ኢመደአ የኢትዮጵያን የሳይበር ደህንነት በማረጋገጥ የሀገሪቷን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ከመደገፍ አንጻር እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።
በቀጣይ ሁለቱ ሀገራት በሌሎች የልማት ዘርፎች ያላቸውን ጠንካራ ትብብር በሳይበር ደህንነት ላይም መድገም እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ለዚህም አምባሳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መግለጻቸውን ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።