ለአፍሪካ አየር ኃይሎች ትብብር መጠናከር የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመሪነት ሚናውን ይወጣል – ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ

AMN-ኅዳር 18/2017 ዓ.ም

ለአፍሪካ አየር ኃይሎች ትብብር መጠናከር የኢትዮጵያ አየር ኃይል የመሪነት ሚናውን ይወጣል ሲሉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 89ኛ የምስረታ በዓሉን “የተከበረች አገር የማይደፈር አየር ኃይል” በሚል መሪ ቃል ህዳር 20 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅት ያከብራል።

በዛሬው ዕለትም የክብረ በዓሉ አካል የሆነው የአፍሪካ አገራት የአየር ኃይል አዛዦች በተገኙበት ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ኃይሎች ፎረም በቢሾፍቱ ከተማ እያተካሄደ ነው።

በፎረሙ የሞሮኮ፣ የዩጋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የማሊ፣ የኬንያ፣ የሩዋንዳ፣ የጂቡቲ፣ የናይጀሪያ፣ የኮንጎ ብራዛቪል እና የኒጀር አየር ኃይል አየር አዛዦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ፤ በዚህ ወቅት እንዳሉት የአቪዮሽን ኢንዱስትሪ ቴክኖሎጂ በየእለቱ እየዘመነና አዳዲስ መልኮችን እየተላበሰ ይገኛል ።

በዚህም የሀገር ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ዘመኑን የዋጀ አየር ኃይል መገንባት እንደሚያሻ ገልፀው፤ ፎረሙ በዘርፉ ያለውን ልምድ እና ተሞክሮ ለመለዋወጥ እንደሚበጅ አብራርተዋል።

በፎረሙም የአፍሪካ አየር ኃይሎች ማህበር ለመመስረት መሰረት የምንጥልበት ነው ብለዋል።

ለአፍሪካ አየር ኃይሎች መጠናከር የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፍሪካ አገራት አቻዎቹ ጋር በትብብር ለመስራት ያለውን ቁርጠኝነት አንስተዋል።

በተለይም በቴክኖሎጂ አቅም ግንባታና በሰው ኃይል ልማት ረገድ አየር ኃይሉ በትብብር እንደሚሰራ ማብራራታቸውን ኢዜአ ዘግቧል

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review