በመዲናዋ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት በተፈፀመ ስርቆት ከ1.6 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱ ተገለጸ

AMN ህዳር 19/2017 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በጥቅምትና ህዳር ወር ብቻ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች በተፈፀመ ስርቆት ከ1.6 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ፡፡

በደቡብ አዲስ አበባ ሪጅን ቡልቡላ አካባቢ፣ ገላን ኮንዶሚኒየም፣ ለቡ ሙዚቃ ቤት እንዲሁም ጀርመን አደባባይ አካባቢ በተፈፀመ የመሰረተ ልማትና የኃይል ስርቆት ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት ደርሷል፡፡

በተመሳሳይ በምስራቅ አዲስ አበባ ሪጅን በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 09 ልዩ ቦታው ብረታ ብረት ፊት ለፊት ከ3 መቶ ሺህ ብር በላይ የሚገመት የትራንስፎርመርና የኃይል ስርቆት መፈጸሙን አገልግሎቱ ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በጉለሌ፣ ኮልፌ፣ አራዳ፣ ቂርቆስና ልደታ ክፍለ ከተሞች በተፈፀመ የኬብልና የሌሎች መሰረተ-ልማቶች ስርቆት ምክንያት ከ2 መቶ ሺህ ብር በላይ ኪሳራ መድረሱንም አመላክቷል፡፡

በአሁኑ ወቅት በመዲናዋ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝም ነው የጠቆመው፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማቶች ላይ በሚፈፀም ስርቆት ወንጀል ምክንያት ለዜጎች ይቀርብ የነበረው የኃይል አቅርቦት በመቋረጡ በዜጎችና በሃገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ መሆኑንም አገልግሎቱ ገልጿል፡፡

በመሆኑም ተቋሙ ከሚወስደው ህጋዊ እርምጃ ባሻገር ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ሀብት የፈሰሰባቸውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ሁልጊዜ በንቃት በመጠበቅ የዜግነት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም ማስገንዘቡን ከአገልግሎቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በ2017 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሩብ ዓመት በኤሌክትሪክ መሰረተ-ልማት ላይ በተፈፀመ ስርቆት ከ2.7 ሚሊየን ብር በላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል፡፡

All reactions:

4444

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review