በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ያደረግነው ሪፎርም ኢትዮጵያን የሚመጥንና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመገንባት ጠንካራ መሰረት የጣለ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

AMN-ኅዳር 19/2017 ዓ.ም

በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ያደረግነው ሪፎርም ኢትዮጵያን የሚመጥንና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመገንባት ጠንካራ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 89ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በነገው ዕለት በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያከብራል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያን እንደ ሀገር በማቆየት ማገርና ምሰሶ ተብለው ከሚጠቀሱ ተቋማት መካከል የጸጥታ ተቋማት ዋነኛዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ ተቋማት ከለውጡ በፊት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደነበሩ አስታውሰው ባለፉት ስድስት ዓመታት በተደረገው ሪፎርም ለሀገር የቆመ ጠንካራና ዘመናዊ ተቋም መገንባት መቻሉን ተናግረዋል።

በጸጥታና ደህንነት ተቋማት የተከናወነው የሪፎርም ስራ ኢትዮጵያን የሚመጥንና ዘመን ተሻጋሪ ተቋማትን ለመገንባት ጠንካራ መሰረት የጣለ መሆኑንም ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 89ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በሚያከብርበት ወቅት ”ጸሐይ-2” የተሰኘችና በአየር ኃይሉ የተሰራች አውሮፕላን ለበረራ ብቁ ማድረጉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

አውሮፕላኗ ግዳጅን በብቃት መፈጸም የሚያስችል ቴክኖሎጂ የታጠቀች ናት ብለዋል።

በለውጡ በተከናወነው ሪፎርምና ስትራቴጂ መሰረት አየር ኃይሉ በሁሉም ረገድ ብቁ እና ዘመናዊ ተቋም መሆን ስለመቻሉም አንስተዋል።

በመሆኑም በ2030 በአፍሪካ ስመጥር አየር ኃይል ለመሆን የያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ በትክክለኛ ጎዳና ላይ መሆኑን የሚያመላክት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በራሷ አየር ኃይል ለመጀመሪያ ጊዜ “ፀሐይ-2” የተባለችውን አውሮፕላን መገጣጠም መቻሏ ታላቅ ስኬት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review