
AMN ህዳር 23/2017 ዓ.ም
በሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ ጨካ እና ጅሩዳዳ ቀበሌ የህብረተሰቡን ሰላም ሲያውኩና ሲዘርፉ የነበሩ የአሸባሪው ሸኔ እና የፅንፈኛው ፋኖ አባላት ለ6ኛ ዕዝ ክፍለ ጦር እጅ መስጠታቸው ተገለፀ።
በቀጠናው የሚገኘው መከታ ክፍለ ጦር አዛዥ ኮሎኔል ጋዳሳ ዲሮ በደራ ወረዳ በተደጋጋሚ ህብረተሰቡን የማወያየት ስራ በመሰራቱ አሸባሪውን ከህዝብ መነጠል እንደተቻለ አብራርተዋል።
ኮሎኔል ጋዲሳ ዲሮ ወደ ሰላም አማራጭ የተመለሱት የሸኔ አባላትና የፋኖ ታጣቂዎች፣ ክላሽ፣ የክላሽጥይት፣ ቦምብና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመያዝ እጃቸውን ለሠራዊቱ መስጠታቸውን ገልፀዋል።
ለሠራዊቱ እጃቸውን የሠጡ የአሸባሪው ሸኔ አመራሮች አብረዋቸው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ ግብረ አበሮቻቸውን ከበርካታ ተተኳሽ እና መሳሪያዎች ጋር እጅ እንዲሰጡ እያደረጉ ይገኛሉ ያሉት ኮሎኔል ጋዲሳ ዲሮ የአሸባሪዎች አደረጃጀት አሁን ላይ እየፈራረሰ እንደሆነም ተናግረዋል።
ክፍለ ጦሩ የተሰጠውን ተልዕኮ በጀግንነት እየፈፀመ እንደሚገኝ የገለፁት ከፍተኛ መኮንኑ የተሰጠውን አማራጭ ተጠቅሞ በሰላም የማይገባ አሸባሪ ቡድን ላይ የሚወስደውን እርምጃ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ፀጥታ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሰለሞን አበበ በበኩላቸው ሠራዊቱ የአሸባሪውን ቡድን አሳዶ በመደምሰስ በደራ ወረዳ እና በአካባቢው አንፃራዊ ሰላም መፍጠር እንደተቻለ አውስተው የሰላም አማራጭን ተጠቅመው በሰላም የሚገቡትን በእንክብካቤ እየተቀበልን ነው ሲሉ መናገራቸውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ የትስስር ገፅ አመልክቷል።