በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች የመረጡትን የሰላም መንገድ ሁሉም ሊከተል ይገባል፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN ኅዳር – 29/2017 ዓ.ም

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ሰላም ከጦርነት ይሻላል በሚል ወደ ሰላም የመጡበትን መንገድ ሁሉም ሊከተል እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለህብረብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአርባምንጭ ከተማ እየተከበረ ነው።

በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል በሺህ የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ሰላም ከጦርነት ይሻላል በሚል ወደ ሰላም መንገድ መምጣታቸውን አስታውሰዋል።

ይህንን መልካም ጅማሮ እና ውሳኔ ሌሎች በተለያዩ አካባቢዎች በትጥቅ ትግል እና በመገዳደል ድል ይገኛል ብለው የሚያምኑ ኃይሎችም እንዲከተሉት ጥሪ አቅርበዋል።

“የሴራ ትጥቃችንን ፈትተን፣ ፍቅርን እና ሰላምን ታጥቀን ኢትዮጵያን ማበልጸግ ቀዳሚ አጀንዳችን ሊሆን ይገባል” ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

ሰላምን በማስቀደም ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ታላቅ ሀገር ሆና ብልጽግናን ለልጆቿ ማሸጋገር እንደትችል እያንዳንዱ ዜጋ የማያልፍ አሻራውን እንዲያሳርፍም መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ብልጽግና የሚረጋገጠው በሥራ ብቻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም አርባምንጭን መመልከት ይቻላል ብለዋል።

ሌሎች በአካባቢው ያሉ ከተሞችም የአርባምንጭን ፈለግ በመከተል ከተማቸውን በማጽዳት እና ዛፍ በመትከል ከተማቸውን እንዲያስውቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

በሰፊና ሁሴን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review