
AMN ታህሳስ 4/2017 ዓም
በአዲስ አበባ ከተማ የፅንፈኛው የሽብር ቡድን ተልዕኮ ለመፈፀም ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አራት ተጠርጣሪዎች በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በተደረገባቸው ጠንካራ ክትትል በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል።
በሽብር ወንጀል የተጠራጠሩት አራቱ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት በአዲስ አበባ ከተማ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ከፅንፈኛው የሽብር ቡድን የወሰዱትን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ 120 የክላሽንኮቭ ጥይት እና ኤፍ ዋን ቦንብ ይዘው ሲንቀሳቀሱ እንደሆነ ነው ፌዴራል ፖሊስ ባወጣው መረጃ ያስታወቀው።
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አባላት ባደረጉት ጠንካራ ክትትል ታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ተጠርጣሪዎቹ እጅ ከፍጅ ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ የምርመራ ቡድኑ መግለጹን ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ሕብረተሰቡ እስከአሁን እያደረገ ላለው ተሳትፎ ምስጋና እያቀረበ፣ ተመሳሳይ የወንጀል ተግባር ሲመለከት የዜጎች ተሳትፎ መተግበሪያን (EFPApp) በመጠቀም ወይም በነፃ የስልክ መስመር 991 በመደወል በፍጥነት ጥቆማ በመስጠት ወይም መረጃውን በአካባቢው ለሚገኙ የፀጥታና ደኅንነት አካላት በአካል በማድረስ የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።