
AMN – ታኅሣሥ -5/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር እየሰጠ ያለውን የሰብዓዊ አገልግሎት ተደራሽነት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባው የማህበሩ የበላይ ጠባቂና የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር 20ኛ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ነው።
በጉባዔው ላይ የማህበሩ የበላይ ጠባቂ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሎሚ በዶ፣ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልና ቀይ ጨረቃ ማህበራት ተወካዮችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በጉባኤው መክፈቻ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ባደረጉት ንግግር ላለፉት 90 ዓመታት ለሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ማህበሩ የሰጠው ሰብዓዊ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
በሂደት ማህበሩ ሃላፊነቱን በብቃት መወጣት የሚያስችለው ቁመና ላይ መሆኑን ጠቅሰው፥ የወደፊቱንም ታሳቢ በማድረግ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ሰብዓዊ አገልግሎቶች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ፈጣን ድጋፍና እገዛ በማድረግም ሃላፊነቱን የመወጣት ጥረቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት አበራ ቶላ፤በኢትዮጵያ ለሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ዓመታትን የተሻገረ መሆኑን ገልጸው፥ በቀጣይም አጠናክሮ ለመቀጠል ተዘጋጅቷል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የቀይ መስቀል እና ቀይ ጨረቃ ንቅናቄ መሰረታዊ መርሆዎች በጠበቀ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ተጎጂ ለሚሆኑ ሰዎች የህይወት አድን ስራ ከማከናወን በተጨማሪ ዘርፈ ብዙ ሰብአዊ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ጊዜ 6 ሚሊዮን አባላትንና 47 ሺህ በጎ ፈቃደኞች እንዳሉት ጠቅሰው፥ በዚህም በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች የሰብዓዊ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
የማህበሩ ያለፉት ሦስት ዓመታት ዓመታዊ ገቢ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህም ለ16 ሚሊዮን ሰዎች በድንገተኛ አደጋ ምላሽ እንዲሁም በአደጋ ሥጋት ቅነሳና መልሶ ማቋቋም ሥራዎች ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።
ማህበሩ በነፃነትና በገለልተኝነት ስራውን እንዲከውን መንግስት በየዓመቱ ሲያደርግ የነበረውን የ5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ወደ 10 ሚሊዮን ብር ማሳደጉንም ጠቅሰዋል።
በተለያዩ የሀገሪቷ አካባቢዎች በሚገኙት ከ80 በላይ የመድኃኒት መደብሮቹ አማካኝነት በዓመት 3 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ መድኃኒት እያቀረበ ይገኛል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ጠቅላላ ጉባዔውን በየሁለት ዓመቱ የሚያካሄደው ማህበሩ የዘንድሮውን ጉባዔ ያለፉት ሦስት ዓመታት የስራ ክንውኖችን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።